Ethiopia Zare's weekly news digest, week 27th, 2012 Ethiopian calendar

ከየካቲት 23 - መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃያ ሰባተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከየካቲት 30 - መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም.):- ሳምንቱ እንዴት ሰነበተ? የሚል ጥያቄ ከተነሣ ከየትኛውም ክስተትና ድርጊት በላይ የኮሮና ቫይረስ በአንድ የ48 ዓመት ጐልማሳ ጃፓናዊ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የሚገልጸው ዜና ለኢትዮጵያ የሳምንቱ ዐቢይ ጉዳይ ነው።

ዓርብ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የጤና ሚኒስትር አስቸኳይ መግለጫ እሰጣለሁ ብሎ የሚዲያ ባለሙያዎችን ሲጠራ፤ ብዙዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል። በእርግጥም የተገመተው ኾነና ኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባት አገር በመኾን እንድትመዘገብ ያደረገው ዜና ተነገረ። ይህ ወሬ ከተሰማበት ቅፅበት ጀምሮ ከዚሁ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ድርጊቶች ታይተዋል። የአገሪቱ ቀዳሚ አጀንዳ የሚኾኑና የሕዝብን ትኩረት ይዘው የነበሩ ጉዳዮች ሁሉ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘትና ተያያዥ ጉዳይ ላይ ኾነ።

ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎች ተስተውለዋል። የሰዎች እንቅስቃሴ ከወትሮው የተለየ እስከመኾን ደርሷል።

ከዚህ ባሻገር በሳምንቱ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ ከአዳዲስ ሹመቶች ጋር በተያያዘ በፓርላማው የነበረው ድባብ አስደማሚ ኾኖ ማለፉ ነው። ሳምንቱን በተለየ እንዲታወስ ያደረገው ሌላው ተያያዥ ጉዳይ በርካታ ሹመቶች በተለያየ መልኩ የተሠጡ መኾኑ ነው። ቀጣዩን ምርጫ 2012 በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያውን የምርጫ ክልሎች ካርታ ይፋ ማድረጉ ከሳምንቱ አንኳር ዜናዎች መካከል አንዱ ነበር።

የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ ትግራይ ውስጥ ድረስልን እየተባልኩ ነው በሚል ያወጣው አጭር መግለጫም ትኩረት ከተሠጣቸው የሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በተለያዩ አቅጣጫዎች የመንግሥት እንቅስቃሴ ጐልቶ የታየበት ነው። በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የዓለም ሕዝብ ግንዛቤ እንዲኖረው ወደተለያዩ አገሮች የኢትዮጵያ ልዑካን እንዲጓዙ የተደረገበት ሳምንት ነበር። ከፍተኛ የአገሪቱ የጦር መኮንኖች ወደ ሱዳን እንዲያቀኑ በማድረግ በህዳሴው ግድብ ላይ መክረዋል።

የቀድሞውና የአሁኗ የአገሪቷ ፕሬዝዳንቶች ለዚሁ ተልእኮ ወደተለያዩ አገሮች እንዲጓዙና በህዳሴ ግድብ ላይ የዓለም ሕዝብ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት የዲፕሎማሲ ሥራ ስለመጀመሩ ያመለከተ ነበር። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ሊቃጣ የሚችል ነገር ካለ፤ የአገር መከላከያ ኃይል በተጠንቀቅ ላይ መኾኑን የአገሪቱ የጦር መኮንኖች የህዳሴ ግድብን በጎበኙበት ወቅት መልእክት ያስተላለፉት በዚሁ ሳምንት ነው። ይህም መንግሥት በዓባይ ወንዝና ተያያዥ ጉዳዮች ጠንከር ያለ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል።

ሌላው በአወዛጋቢነቱ ሊጠቀስ የሚችለው ማርች 8ን ተንተርሶ ኦፌኮ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በአንዲት ወጣት በኩል የተላለፈ ንግግር ነው። ይህንን አደገኛ የተባለ ንግግር ደግሞ ያሠራጨው OMN ነው። በብዙኀኑ ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰው ይህ ንግግር የአገሪቱ ፖለቲካ በቤተሰብ መሐል ጭምር እንዲገባ መፈለጉን የሚያሳይ ነው ተብሏል። ይህ ጉዳይ በሰዎች አስተያየት ብቻ የተገደበ ሳይኾን፤ መንግሥት በይፋ እንዲህ ያለውን ድርጊት አንታገስም ያለበት ሳምንት ነበር። በዚህ ጉዳይ የተፈጠረው ውዝግብ አሁንም አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል። ይህ የአገራችንን የፖለቲካ አካሔድ “በመናገር ነፃነት” ስም እየኾነ ያለውን ድርጊት መፈተሽ እና አደብ ማስያዝ ያስፈልጋል በሚል ብዙ አስተያየቶች የተሠጡበት ሲሆን፤ መንግሥትም ይህንኑ ንግግር መሠረት በማድረግ የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ያለበት ኾኗል።

በዚህ ሳምንት የእነ አቶ በረከት ስምኦን ጉዳይ በችሎታ የታየበት ነው። ወደ ሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም 1.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንደተደረገለት በማሳወቅ ይህንኑ ላደረጉ የንግዱ ሕብረተሰብ አባላትና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና የቀረበበት ነው። ይህ የመጀመሪያ ዙር መኾኑ የተገለጸ ሲሆን፤ 1.3 ቢሊዮን ብሩ በካሽ ገቢ መደረጉ ተገልጿል። በዐይነትም 2600 የቀንድ እና የጋማ ከብቶች ስጦታ እንደተሠጠ የተገለጸበት ነው። በዚህ ፕሮግራም ላይ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድም የሠጣችሁትን በእጥፍ እንድታገኙ እንሠራለን ብለዋል። ድጋፉ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል ስለመገኘቱም ተገልጿል።

ከሳምንቱ የቢዝነስ ኢኮኖሚ ዜናዎች ውስጥ የዳያስፖራ ባንክ ለማቋቋም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩ ይጠቅሳል። እንዲህ ካሉት ከሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ የተወሰኑትን ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን በማከል በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።

አሳሳቢው ኮሮና በኢትዮጵያ

ዓርብ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ከጤና ሚኒስቴር የተሰማው አንድ ዜና ለኢትዮጵያውያን አስደንጋጭ ነበር። የጤና ሚኒስትር ኾነው በተሾሙ ማግስት በዕለቱ የተሰማውን አስደንጋጭ ወሬ ይዘው ለቀረቡት ለጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰም ቢኾን በመልካም የሚታይ አልነበረም። የመጀመሪያ መግለጫቸውን በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው በመንገር መጀመራቸው ጥሩ አጋጣሚ አልነበረም።

ይሁን እንጂ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ አንድ ጃፓናዊ መገኘቱን መግለጽ ነበረባቸውና ይህንኑ እወቁ ብለው ከዚህ ወረርሽኝ እንጠበቅ ዘንድ ሞያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል። ቫይረሱ ስለተገኘበት ጃፓናዊውም ተጨማሪ ማብራሪያ ሠጥተዋል፡ ዶክተር ሊያ በዚያ መግለጫቸው መንግሥታቸው ኮሮናን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ዝግጅት በሚገባ አብራርተዋል። ዋናው ነገር ግን ራስን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ሁሉም በየግሉ ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ ወሳኝ መኾኑንና መደናገጥም እንደማያስፈልግ አመላክተዋል።

ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ ግን በብዙዎች ዘንድ ድንጋጤ መፍጠሩ አልቀረም። በዕለቱ በሥራ ገበታቸው ላይ የነበሩ ሰዎች ስሜት ሲለዋወጥ በግልጽ ይታይ ነበር። በደቂቃዎች ቅፅፈት ሰዎች ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የሚያደርጉት የስልክ ልውውጥ የአገሪቱን የሞባይል ኔትዎርክ አጨናንቆ በቀላሉ ለመደማመጥ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱ፤ የዕለቱ ዜና በእርግጥም አስደንጋጭ እንደነበር ያሳያል። ከመግለጫው መረዳት እንደሚቻለው በኮሮና ቫይረስ የተጠቃውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኾኖ የተመዘገበው ጃፓናዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘጠኝ ቀናት የቆየ ሲሆን፤ ከእርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ማቆያ መግባታቸውና ምርመራ ተደርጎላቸዋል። እስካሁን ሁለቱ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ከዓርብ ዜና በኋላ የጉዳዩ አነጋጋሪነት አሁንም ድረስ የቀጠለ ሲሆን፤ በተለይ ዜናውን ተከትሎ የግብይት ሥርዓቱን መረበሹ ቀዳሚ ክስተት ኾኗል።

ከዜናው መነገር በኋላ ሰዎች በአንፃራዊነት ወደተረጋጋ ሁኔታ ሲገቡ፤ ቫይረሱን ለመከላከል ያግዛሉ የተባሉትን እንደ አፍ ማስክ ያሉ ዕቃዎችን ለመሸመት መሯሯጣቸው ነበር። ብዙዎች እነዚህን ዕቃዎች ገበያ ላይ ለማግኘት ከባድ እንደኾነባቸው መግለጽ የጀመሩት በዚያው ዕለት ነበር። ቢገኝ እንኳን በቅፅፈት ዋጋቸው የሌላ ዕቃ ዋጋ እንጂ በትክክል የዕቃዎቹ ዋጋ ነው የሚያስብል አልነበረም።

በተለይ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ የአፍ ማስክ፣ የእጅ ማፅጃ አልኮል እና ተመሳሳይ አገልግሎት ይሠጣሉ የተባሉ ዕቃዎች ከመደበኛው ዋጋ በላይ መሸጥ ጀመሩ። እንደምሳሌ የሚጠቀሰው ከ50 – 55 ብር ይሸጥ የበረ የእጅ ማበሻ አልኮል ከ120 - 200 ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ የአፍ ማስክ ደግሞ ከአንድ መቶ ብር በላይ ሲሸጥ ታይቷል። የአፍ ማበሻ የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ እንዲህ ባልገነነበት ወቅት ከ10 ብር ያነሰ ዋጋ የነበረው ነው። ከዓርብ ጀምሮ ግን አንዳንዶች ዋጋውን እጅግ በማናር ሲሸጡ የታየበት ሁኔታ ገበያውን ሲረብሽ ታይቷል።

ፋርማሲ የለም የተባለ የአፍ ማስክ መንገድ ላይ እስከ 150 ብር እየተሸጠ መኾኑ በአሳዛኝነቱ የሚታይ ድርጊት ኾኗል። ፈጽሞ ተቀባይነት በሌለው ዋጋ ግብይት እየፈጸሙ ያሉት እነዚህ ምርቶች ብቻ ሳይኾኑ፤ ምግብ ነክ ምርቶችንም በብዛት መሸመታቸው የአንዳንድ ሱፐር ማርኬቶችን መደርደሪያዎች ባዶ አድርጓል። በመደበኛ መደብሮች ሳይቀር እንደ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ዘይትና የመሳሰሉ ምርቶች ፈላጊያቸው በመብዛቱ ዋጋ እየጨመሩ መሸጥ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተስተውለዋል።

የሰዎች የመግዛት ፍላጐት የአንዳንድ ነጋዴዎች ተፈላጊ ናቸው ባሉዋቸው ዕቃዎች ላይ ያደረጉት የዋጋ ጭማሪን ተከትሎ ግን መንግሥት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻውን መግለጫ አውጥቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ዋጋ የሚጨምሩትን ለመቅጣት አንድ ግብረ ኃይል ይቋቋመ ሲሆን፤ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቷል። ይሁንና አሁንም አንዳንድ ቦታ የሚታየው ነገር ብዙም የተለወጠ አይደለም።

የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትሩ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተጋነነ ዋጋ የሚጠይቁ ድርጅቶችን ለመቆጣጠርና አቅርቦትን ለማሻሻል የተደራጀው ግብረ ኃይል ወደ ሥራ እንደሚያስገባ ገልፆ፤ እጥረት ያለባቸውን ምርቶችም የሚያቀርብበት መንገድ እንደሚያመቻች አሳውቋል።

ሌላው ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሕብረተሰቡ እንዲረጋጋና ራሱን እንዲጠብቅ የተለያዩ መልእክቶች እየተላለፉ ነው። የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰት አስደንጋጭ ቢኾንም፤ ሁኔታው በዓለም የመጣ በመኾኑ ድንጋጤውን ተወት አድርጐ ቫይረሱን ለመከላከል መሥራት የሚገባ መኾኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች በሰፊው እየተሠራጩ መምጣታቸው በበጐ የሚታይ ተግባር ኾኗል።

ብዙ የመገናኛ ብዙኀንና የማኅበራዊ ሚዲያዎች ቫይረሱን ለመከላከል መደረግ አለባቸው ተብለው በባለሙያዎች የሚመከሩ መልእክቶችን ማስተላለፋቸው በበጐ የሚታይ፤ ከዚህም በኋላ መቀጠል ያለበት ነው። ከዚህ ባለፈ ግን ጐላ ብሎ የታየው ገበያ ውስጥ ምስቅልቅል የመፍጠሩ ጉዳይ ከወዲሁ ታስቦበት ሊሠራ እንደሚገባ እየተነገረ ነው።

ከተለመደው የግብይት ሥርዓት ወጣ ብሎ የታየው ርብርብ ጐልቶ ታይቶ ነበርና መንግሥትም፤ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ለማውጣት ጊዜ ባይፈጅበትም፤ ዋናው ነገር ገበያው የከፋ ነገር እንዳያመጣ መሥራት አስፈላጊ መኾኑን አስተያየት እየተሠጠ ነው።

ከዚህ ቫይረስ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሚደረገውን መከላከል ለማጠናከር ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ ክልሎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላት የተዘጋጀ ሲሆን፤ መንግሥት 300 ሚሊዮን ብር መበጀቱም ተገልጿል።

ብልጽግና ፓርቲም አዘጋጅቶት በነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ካገኘው ገንዘብ 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለጹት፤ 100 ሚሊዮን ብሩ የጤና ሚኒስቴር ቫይረሱን ለመከላከል የንጽህና መጠበቂያ ለማሟላት ለሚያደርገው ጥረት የሚውል ሲሆን፤ በተለይ አቅም ለሌላቸው ድጋፍ የሚውል ስለመኾኑ ተጠቅሷል።

እስከ እሁድ ማታ ድረስ በነበሩ መረጃዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች አራት ደርሰዋል። መጋቢት 6 ቀን 2012 የጤና ሚኒስትር እንዳስታወቀው ሦስት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው ቁጥሩን አራት አድርሶታል።

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የ42 ዓመት ኢትዮጵያዊ እንደኾነም ታውቋል። ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡት ሦስቱ ሰዎች ዓርብ ዕለት በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠው ጃፓናዊ ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው። ከዚህ ጃፓናዊ ጋር ተገናኝተው የነበሩት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊም ለይቶ ማቆያ ገብተዋል። (ኢዛ)

የምርጫ ካርታውና የፖለቲካ ፓርቲዎች

ከጥቂት ወራት በኋላ ይካሔዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የምርጫ ክልሎች ካርታን ይፋ ያደገው በዚህ ሳምንት ነው።

ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ክልሎችን የሚያመላክተው ካርታ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡበት ነበር። እያንዳንዱ ክልልና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ለፌዴራል ምክር ቤት የሚኖራቸው የምርጫ ክልሎችን የተገለጸበት ሲሆን፤ ቦርዱ ባሳወቀው መሠረት ትግራይ 38፣ አፋር 8፣ አማራ 138፣ ኦሮሚያ 178፣ ሶማሌ 23፣ ቤንሻንጉል 9፣ ደቡብ 123፣ ጋምቤላ 3፣ ሐረሬ 2፣ ድሬዳዋ 2 እና አዲስ አበባ 23 ለፌደራል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ይኖራቸዋል። ነገር ግን የክልል ምርጫው በቀደመው አከላለል መሠረት የተካሔደ መኾኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በካርታ ይፋ የምርጫ ክልል ኖሮት እንደማያውቅና ይህ የመጀመሪያው የምርጫ ክልሎችን የሚያሳይ ካርታ እንደኾነ ካርታው ይፋ በኾነበት ወቅት የገለጹ ሲሆን፤ አሁን በካርታ እንዲመላከት መደረጉ አዲስ ነው ብለዋል። ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንደተሰማው ቀድሞ የምርጫ ክልሉ ይህ ነው ይባልና በትክክል ለመለየት የማያስችል እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ግን የትኛው የምርጫ ጣቢያ በየትኛው ክልል እንደሚያርፍ የሚያሳይ በመኾኑ በመልካም የሚታይ እንደኾነ ገልጸዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን በበኩላቸው አሁን የተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች በ1976 ዓ.ም. በደርግ ዘመን የተካሔደውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት ያደረገና በ1985 መካለላቸውንም ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል። በዚሁ ካርታ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሠጥተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን፤ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የሲዳማ ጉዳይ ነው። ይህ ጥያቄ የቀረበው በኦፌኮ አቶ በቀለ ገርባ ነበር። የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የተደረገና ክልል የመኾን ድምፅ የተሠጠ ሲሆን፤ አሁን ይፋ በተደረገው የምርጫ ካርታ እንደ ክልል ታይቶ ካርታው ይዘጋጃል ብለው መጠበቃቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ጉዳይ እንዴት ነው ብለዋል።

ወይዘሪት ብርቱካንም “እኛ የራሳችንን መርጠናል” ብለዋል። በተዘጋጀው ካርታ መሠረት በሁሉም ምርጫ የአገሪቱ ምርጫው የሚካሔድ መኾኑንና ምርጫ የማይካሔድበት የአገሪቱ ክፍል እንደማይኖርም አሳውቀዋል። (ኢዛ)

ቢሊዮን ብር የተገኘበት ብልጽግናና የገቢ ማሰባሰቢያ

ከሳምንቱ ዜና ተጠቃሽ የሚኾነው ሌላው ዜና የብልጽግና ፓርቲ ያዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም 1.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ማሳወቁ ነው። መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገው ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በአገሪቱ የሚታወቁ ትላልቅ ኩባንያዎችና ታዋቂ ባለሀብቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልፆ፤ በፓርቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እውቅና ተሠጥቷቸዋል።

በዕለቱ እንደተገለጸውም በመጀመሪያው የድጋፍ ፕሮግራም 1.5 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሰባሰበ ሲሆን፤ 1.3 ቢሊዮን ብሩ በጥሬ ገንዘብ ገቢ ኾኗል። 2600 የጋማና የቀንድ ከብት ለብልጽግና ፓርቲ መሠጠቱ ተገልጿል። ለፓርቲው ድጋፍ ማድረጋቸው ከተገለጹ ኩባንያዎች ውስጥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ ይዟል።

በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከፍተኛውን ድጋፍ የሠጠው ሜድሮክ ኢትዮጵያ ነው። ሜድሮክ ኢትዮጵያ የሠጠው ድጋፍ 100 ሚሊዮን ብር ነው።

ከሜድሮክ ሌላ ከፍተኛውን የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት የፋይናንስ ተቋማት ናቸው። በዕለቱ ድጋፍ ካደረጉት መካከል ቀዳሚነቱን የያዙት አዋሽ ባንክ እና ዳሸን ባንኮች ናቸው። እነዚህ ሁለት ባንኮች እያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሠጥተዋል።

ከሁለቱ ባንኮች ሌላ ከ10 - 15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የሠጡት ባንኮች የኦሮሚያ የሕብረት ሥራ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ንብ ባንክ፣ ሕብረት ባንክ፣ ብርሃን ባንክና ሌሎች ባንኮች ናቸው።

ከኢንሹራንስ ኩባንያዎችም እንደ አዋሽ ኢንሹራንስ፣ ናይስ ኢንሹራንስ፣ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

በዕለቱ እንደተገለጸው ኖክ እና ታዋቂው ነጋዴ አቶ በላይነህ ክንዴ እያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ብር ሠጥተዋል።

ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ለብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ ካደረጉት ውስጥ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን፣ ረሃማ ኮንስትራክሽን፣ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን፣ ተክለብርሃን አንባዬ ኮንስትራክሽን፣ አሰር ኮንስትራክሽን፣ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ ሀስንና ንኮማድ ኮንስትራክሽን ይገኙበታል። እነዚህ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጋቸው ታውቋል። ሌሎች የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በተመሳሳይ የተለያየ መጠን ያለው ድጋፍ ማድረጋቸውን ለመገንዘብ ተችሏል።

የብልጽግና ፓርቲ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በዕለቱ ማግኘቱ የተገለጸው የገንዘብ መጠን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ ማሰባሰብ የቻለው ከፍተኛው የገንዘብ መጠን ነው እየተባለ ነው። የብልጽግና ፓርቲም በፌስቡክ ገጹ “የትናንት ምሽቱ ዝግጅት ልዩ ነበር፣ ብልጽግና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በይፋ ጀምሯል። በመጀመሪያው መርሃ ግብሩም 1.5 ቢሊዮን ብርና 2,600 የቁም እንስሳትን በመሰብሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ተአምር ሠርቷል” ብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ