የ2012 ዓ.ም. 18ኛ ሳምንት አንኳር ወሬዎች
ከታኅሣሥ 27 - ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ
የዓመቱ አሥራ ስምንተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች
ኢዛ (ከታኅሣሥ 27 - ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ባሳለፍነው ሳምንት ጐልተው ከሚጠቀሱ ዜናዎች ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን ማጽደቁ አንዱ ነው። በዚህ አዋጅ እንደ ሴንጢ፣ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ … የመሳሰሉትን አደገኛ በኾነ ሁኔታ መገልገልና በብዛት መያዝ ክልከላ የተደረገበት መኾኑን የሚያመለክት አንቀጽ ያለው ነው። ያለፍቃድ ዘመናዊ ከኾኑ መሣሪያዎች ከጦር ሜዳ መነፅር ጀምሮ የተለያዩ መሣሪያዎችን መያዝ ማከማቸት ማምረትና ማዘዋወር እንደማይቻልም ይደነግጋል።
የጦር መሣሪያ ፍቃድ አሠጣጥ እነማን ፍቃድ ማግኘት እንደሚችሉና ሌሎች ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው። በዚህ አዋጅ የተቀመጡት ክልከላዎችን የተላለፈ፣ ያለፈቃድ መሣሪያዎችን የያዘና ሌሎች በአዋጁ ውስጥ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የተላለፈ ማንኛውም ሰው በሕግ ተጠያቂ የሚኾንበትንና የቅጣት መጠኑንም የሚያስቀምጥ ነው።
ይህ ዜና በተሰማ ማግስት ግን ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ 52 ክላሽንኮቭ የመያዙ ዜናም ካሳለፍነው ሳምንት ክስተቶች ውስጥ አንዱ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝትና በዚያ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደኅንነት ከደቡብ አፍሪካ አቻቸው ጋር ስለመስማማታቸው የተገለጸውም ባሳለፍነው ሳምንት ነው።
ከሳምንቱ ዜናዎች የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በአዲስ አበባ ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ ነው። ግብጽ ይዛ በመጣችው አዲስ ሐሳብ ምክንያት ውይይቱ ያለፍሬ ቀርቷል። ይህም ቢሆን ግን አገራቱ በዋሽንግተን ውይይት ለማድረግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ወደዚያው ሔደዋል። ዛሬ (ሰኞ ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል።
እንዲህ ያሉ ክስተቶች የተስተዋሉበት ያሳለፍነው ሳምንት ወሬዎች ውስጥ የተወሰኑት እንዲህ ቀርበዋል።
የጦር መሣሪያን ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር አዲስ አዋጅ ጸደቀ
ከሳምንቱ ዜናዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ማጽደቁ ይጠቀሳል። በዚህም የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር የአገርንና የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ስለመዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን፤ አዋጁ የተለያዩ ድንጋጌዎች አካቷል። የዜጎችንና የሕዝቦችን መብትና ደኅንነት ለማስከበር አስፈላጊ መኾኑን በመገንዘብ ጭምር አዋጁ ስለመዘጋጀቱ በምክር ቤቱ ተብራርቷል።
ግለሰቦች የታጠቋቸውን የጦር መሣሪያዎች የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ተግባር ሊውሉ የሚችሉበትን እድል መፍጠር አስፈላጊ በመኾኑ ጭምር ስለመዘጋጀቱም በተጨማሪ ተጠቅሷል።
የጦር መሣሪያ ፍቃድ አሠጣጡን በተመለከተ እነማን ፍቃድ ማግኘት እንደሚችሉና ሌሎች ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው። በዚህ አዋጅ የተቀመጡትን ክልከላዎች የተላለፈ፣ ያለፈቃድ መሣሪያዎችን የያዘና ሌሎች በአዋጁ ውስጥ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የተላለፈ ማንኛውም ሰው በሕግ ተጠያቂ የሚሆንባቸውን የቅጣት መጠኑንም አስቀምጧል።
ይህ ዜና በተሰማ ማግስት ግን ወደ አዲስ አበባ ሲገባ የነበረው 52 ክላሽንኮዥ የመያዙ ዜናም ካሳለፍነው ሳምንት ክስተቶች ውስጥ አንዱ ነው።
ማንኛውም ዐይነት የጦር መሣሪያ፣ ብዛት ያላቸው ጉዳት አድራሽ ስለቶችና ተያያዥነት ያላቸውን የመሣሪያው መገልገያዎችን የሚመለከተው ይህ አዋጅ፤ ከፍቃድ ውጪ የጦር መሣሪያ፣ የጉዳት ማድረሻ ዕቃ፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ በጦር መሣሪያ ላይ ሊገጠም የሚችል ማንኛውም ዐይነት መነጽር ወደ አገር ማስገባት፣ ከአገር ማውጣት፣ መያዝ፣ መስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሠልጠንና ማስወገድ ክልክል መኾኑን ያመለክታል።
እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ ሴንጢ፣ አስለቃሽ ጭስና ኬሚካሎች ለሕብረተሰቡ አደገኛ በኾነ ሁኔታ መገልገልና በብዛት ይዞ መገኘትም ክልከላ የተጣለበት እንደኾነ በአዋጁ ተቀምጧል።
የጦር መሣሪያ ፍቃድ ያላቸው አካላት ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው አካባቢ መገኘት እንደማይኖርባቸው ይኸው በዚህ ሳምንት የጸደቀው አዋጅ ደንግጓል። ከዚህም ሌላ በምርጫ ቦርድ በተከለከሉ ስፍራዎች፣ በሕዝብ መዝናኛና በስፖርት ማዘውተሪያ፣ በትምህርትና ሃይማኖት ተቋማትና መሰል የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘትን አዋጁ ይከለክላል።
እንደ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖትና የእምነት ተቋማት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማኅበራት እንዲሁም የትምህርት ተቋማት የጦር መሣሪያ ፍቃድ የማይሠጣቸው መኾኑም በአዋጁ ተመልክቷል።
በዚህ አዋጅ መሠረት ቀደም ብለው የታጠቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች የታጠቁት የጦር መሣሪያ ያለተከለከለ እስከኾነ ድረስ በአንድ ዓመት የሽግግር ጊዜ ተቆጣጣሪው ተቋም በአካባቢያቸው ተገኝቶ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ቀርበው ሕጋዊ ማድረግ እንደሚኖባቸው ይደነግጋል።
በጊዜ ገደቡ ውስጥ ፍቃድ ያልወጣበት የጦር መሣሪያ ግን በተቆጣጣሪው የሚወረስ መኾኑን አዋጁ ይደነግጋል።
ከጦር መሣሪያ ፍቃድ አሠጣጥ ጋር በተያያዘም አነስተኛ ወይም ቀላል መሣሪያን ለአንድ ሰው አንድ ብቻ የሚፈቅድ ነው።
ፍቃድ ለማግኘት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችም አዋጁ በዝርዝር ይዟል። ይህንን አዋጅ በተላለፉት ላይ ስለሚጣል ቅጣትም ማንኛውም ሰው በአዋጁ የተመለከተውን ክልከላና ግዴታ በመተላለፍ የጸናና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሣሪያዎችን ያስቀመጠ፣ የያዘ፣ ያመረተ፣ ከአገር ያወጣና ያስገባ መሰል ክልከላዎችን ሲተላለፍ እስከ ሦስት ዓመትና ጽኑ እስራት እንዲሁም እስከ 10 ሺሕ ብር ድረስ ሊቀጣ እንደሚችል ይደነግጋል።
የጦር መሣሪያዎችን ይዞ ከመገኘት ጋር ያሉ የሕግ መተላለፍ እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም እስከ 100 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልበት የደነገገ አንቀጽ ያለው ነው። (ኢዛ)
አዲስ አበባ መግቢያ ላይ የተያዙት ክላሽንኮቮች
በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወር የጦር መሣሪያ ስለመያዙ የሚገልጹ ዘገባዎች በተደጋጋሚ መስማት የተለመደ ሆኗል ማለት ይቻላል። እንዲህ ያለው ሕገወጥ ተግባር ዓላማው ምንድነው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሲሆን፣ ምናልባትም ሾልከው የገቡ መሣሪያዎች ቢኖሩስ? ብሎ ስጋት ሊያጭር ይችላል። ይህም ሆኖ ግን በሕገወጥ መንገድ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሲዘዋወር ስለሚያዝ የጦር መማሪያ አሁንም መሰማቱ ቀጥሏል። ባሳለፍነው ሳምንትም ከተሰሙ ዜናዎች አንዱ ወደ አዲስ አበባ በረቀቀ መንገድ የጦር መሣሪያ ሊገባ ሲል ተይዟል።
በሕገወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሊገባ የነበረው ሕገወጥ የጦር መሣሪያ የተያዘው ደግሞ ሰበታ ላይ ነው።
ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ተያዘ የተባለው የጦር መሣሪያ 52 ክላሽንኮቭ ነው። 52ቱ ክላሽንካች በአንድ አይሱዙ የጭነት መኪና ላይ በረቀቀ መንገድ በመደበቅ በተዘጋጀ ስፍራ ጭኖ ሲጓዝ እንደነበር የሰበታ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ያስታወቀ ሲሆን፣ የጸጥታ አካላት ባደረጉት ፍተሻ የጦር መሣሪያዎቹ ሊያዙ ችለዋል።
እነዚህ የጦር መሣሪያዎች የተያዙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ በጸደቀ ማግስት መኾኑ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል። (ኢዛ)
ዶ/ር ዐቢይ በደቡብ አፍሪካ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት አድርገዋል። በተለይ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ያገኙበት ነበር።
ይህ ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጉዳይ ዙሪያ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር መምከራቸውንና ኢትዮጵያውያን ዜጎች በአገሪቱ ሁለንተናዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሠጣቸው ለፕሬዝዳንቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን በጁሐንስበርግ ኢምፔሪያል ዎንደርሰን ክሪኬት ስቴዲየም ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን አብስረዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚደርስባቸውን ችግር ለመፍታት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ ስለመሥጠታቸውም ተገልጿል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ኮሚቴ አቋቁሞ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርስን ማንኛውንም ችግር በማጣራት እርምጃ እንደሚወስድ ቃል የገባ ስለመኾኑም ዶ/ር ዐቢይ ለኢትዮጵያውያኑ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ከተደረሰበት ስምምነት ባሻገር ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከተወያዩ በኋላ፤ አገራቱ የተለያዩ ስምምነቶችንና የመግባቢያ ሰነዶችን መፈራረማቸው ተገልጿል።
በተለይ በጤናና በቱሪዝም መስክ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት የሁለቱ አገራት መሪዎች ተፈራርመዋል።
የሁለቱ አገራት መሪዎች በጋራ በሠጡት መግለጫ ላይ፤ በተለይ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ችግሩን ለመፍታታ መስማማታቸውን ዶ/ር ዐቢይ ገልጸው፤ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳይን በፍጥነት ለመፍታት የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚገኙባቸው የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች መስማማታቸውን በጋራ መግለጫው ላይ ተናግረዋል። (ኢዛ)
“ብልጽግና ፓርቲ የቆመባቸው ምሰሶዎች ፌዴራሊዝሙን የሚጠብቁና የሚንከባከቡ ናቸው” አቶ ንጉሡ ጥላሁን
በሳምንቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ በብልጽግና ፓርቲ ዙሪያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሴክሬተሪያት የሠጡት ማብራሪያ ይጠቀሳል። ብልጽግና ፓርቲ “የቆመባቸው ምሰሶዎች ፌዴራሊዝሙን የሚጠብቁና የሚንከባከቡ ናቸው” ያሉት አቶ ንጉሡ፤ ሰሞኑን እንደገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ግብ የኢትዮጵያዊያን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ፣ ሥነ አእምሮአዊና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታን ባካተተ መልኩ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ነው በማለትም ተናግረዋል።
የብልጽግና እሴቶች ተብለው የሚጠቀሱት ሕብረ አገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብርና ነፃነት መኾናቸውን የጠቀሱት አቶ ንጉሡ፣ “ኢትዮጵያ አሃዳዊነትን ላትመልስ ሸኝታዋለች። ይህ ዐይነቱ ሥርዓት ሊታሰብ አይችልም።” በማለት የፓርቲያቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
ፌዴራላዊ ሥርዓቱን በማፍረስ አሃዳዊነትን መገንባት የማይታሰብ መኾኑን ያመለከቱት አቶ ንጉሡ አሃዳዊነት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚንድ መኾኑንም ጠቁመዋል።
አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና እውነተኛውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለመገንባት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ፤ ሕግብረ ብሔራዊ አንድነት ከሰው ልጆች ባሕርይ ተነስቶ ወደ አገራዊ ባሕርይ ጎልብቶ የሚያድግ መኾኑንም ተናግረዋል።
ብልጽግና የዜጎችን ክብር የሚያረጋግጥ መኾኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን የግለሰብና የቡድን መብታቸው የሚከበርበት ግለሰባዊና ተቋማዊ ጭቆናዎች የሚወገዱበት ሥርዓት እንደሚያሰፍን የተናገሩት አቶ ንጉሡ፤ ፓርቲያቸው ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅኝት ስለመውጣቱ በይፋ ያረጋገጡበት በሰሞኑ ማብራሪያቸው፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅኝት ትመራበት በነበረበት ወቅት ያጧቸውን እሴቶች በመመለስ፣ ያገኘችውን መልካም ጐኖች ለማስቀጠል መሥራት አስፈላጊ መኾኑን አመልክተዋል። (ኢዛ)
እነአቶ በረከት ስምኦን ለተመሠረተባቸው ክስ የመከላከያ ማስረጃ አቀረቡ
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸውን በፍ/ቤት እየተከታተሉ ያሉት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ዓቃቤ ሕግ ለመሠረተባቸው ክስ የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡት በተጠናቀቀው ሳምንት ነበር።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የቀረቡት በተከሰሱባቸው ክሶች ላይ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተሠጥቶ በነበረው ትእዛዝ ሲሆን፣ የመከላከያ ማስረጃ ሰነድና አሉን ካሏቸው አሥራ አንድ የቃል ምስክሮች ውስጥ ሦስቱን እንዳቀረቡ ተገልጿል።
የተከሳሽ ጠበቆች በአንደኛው ክስ ካቀረቧቸው አራት የቃል ምስክሮች አንዱ በማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፣ በሁለተኛው ክስ ላይ ደግሞ በጽሑፍ ያቀረቧቸው የቃል ምስክሮች ግን ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ጠበቆች የቃልና የሰነድ የመከላከያ ማስረጃቸውን ለፍርድ ቤት ሲያስገቡ፤ ለዓቃቤ ሕግ በተገቢው ጊዜ እንዳልሠጡ ለፍርድ ቤቱ ገልፆ፤ ይህም በመኾኑ የቃል ምስክሮች ከሰነዶች ተነስተው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሠጡ ስለሚችሉ ሰነዶችን መርምሮ ለመከራከር ተለዋጭ ቀጠሮ ይሠጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የእነ አቶ በረከት ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ምስክሮቹ ከአዲስ አበባ የመጡ መኾናቸውን በመጥቀስ፤ ለአላስፈላጊ ወጪ እንዳይዳረጉ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሠጡ ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፤ ፍርድ ቤትም እነ አቶ በረከት ጠበቆች የቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት ዳኞች ባቀረቡበት ዕለት ለዓቃቤ ሕግም ማቅረብ እንደነበረባቸው በመግለጽ፤ ምስክሮች ቃላቸውን በተለዋጭ ቀጠሮ እንደሚሠጡ በማስገንዘብ ለጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሠጥቷል። (ኢዛ)
ግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ይዛ የቀረበችው ሐሳብ በኢትዮጵያ ተቀባይነት አጣ
ከሳምንቱ ዐቢይ ዜናዎች ውስጥ በቀዳሚነት ሊቀመጥ የሚችለው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ ሲያካሒዱት የቆዩት ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ ነው። ይህ ብዙ ተስፋ ተደርጐበት የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ ከተሠጠው መግለጫ እንደተረጋገጠው ግብጽ ይዛ የቀረበችው አዲስ ሐሳብ ተቀባይነት በማጣቱ ነው።
በአዲስ አበባ የተካሔደውን የሦስቱ አገራት ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሠጡት መግለጫ፤ ውይይቱ ያለስምምነት የተጠናቀቀው ግብጽ የግድቡን የውኃ ሙሌት በተለከተ አዲስ ሐሳብ ይዛ በመቅረቧ መኾኑን አስታውቀው፤ ግብጽ ግድቡ ከ12 እስከ 21 ዓመት እንዲሞላ የሚል አዲስ ሐሳብ ማቅረቧ ፤ኢትዮጵያ ይህን ሐሳብ በማንኛውም መልኩ እንደማትቀበል በመግለጿ ውይይቱ ያለስምምነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ከዚህ ቀደም የህዳሴው ግድብ በሰባት ዓመት ውስጥ እንዲሞላ ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም፤ አዲሱ የግብጽ ሐሳብ ውይይቱን እንዳይሳካ አድርጓል።
የሦስትዮሽ ውይይቱ በዚህ መልኩ ያለስምምነት መጠናቀቁ በግድቡ ዙሪያ ያለውን የጋራ የምክክር መድረክ የሚያወሳስበው መኾኑን እያመላከተ ነው። ይህም ቢሆን ግን ወደ ስምምነት ለመምጣት ቀጣይ ውይይቶች የሚጠበቁ ሲሆን፤ እስካሁን የተደረጉትን የሦስትዮሽ ውይይቶች የሦስቱም አገራት ተወያዮች ለየአገራቸው መሪዎች ሪፖርት ካደረጉ በኋለ ቀጣይ ስብሰባቸውን ወደ አሜሪካ በማቅናት ያደርጋሉ ተብሏል።
ሚኒስትሮቹ ዛሬ ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ በማምራት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ በተገኙበት በተካሔዱት አራት የቴክኒክ ስብሰባዎች ዙሪያ ይገለጻል ተብሎም ይጠበቃል።
በዛሬው ዕለት በዋሽንግተን በሚደረገው ውይይት ላይ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚገኙ ታውቋል። (ኢዛ)



