አዲሷ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ
አዲሷ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ሹመታቸውን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሲያቀርቡ
በዚህ ወቅት የአሜሪካ እገዛ እንደሚያስፈልግ አምባሳደር ሬድዋን ገለጹ
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 1, 2021)፦ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር በመኾን የተሾሙት አዲሷ አምባሳደር የሹመት ደብዳቤያቸውን ማቅረባቸው ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር በመኾን የተሾሙት ጊታ ፓሲን የሹመት ደብዳቤ ቅጂያቸውን ያቀረቡት በዛሬው ዕለት (ሰኞ የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም.) ሲሆን፣ ይህንንም ሹመት ደብዳቤ ቅጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተቀብለዋል።
የሹመት ደብዳቤው በቀረበበት ወቅት አዲሷ አምባሳደር የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በማጠናከሩ ረገድ አምባሳደሯ የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ በአምባሳደር ሬድዋን ተጠይቋል።
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር የወዳጅ አገራት በተለይም የአሜሪካ ትብብር አስፈላጊ መኾኑንም አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ስለመምከራቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የሕወሓት ቡድን ሲፈጥራቸው የነበሩ ችግሮችንና በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ የተወሰደበትን ምክንያትም አምባሳደር ሬድዋን ለአዲሷ የአሜሪካ አምባሳደር በዝርዝር ማቅረባቸውም ታውቋል።
አዲሷ የአሜሪካ አምባሳደር የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ወዳጅ በመኾን የሚታወቁ መኾናቸው የሚነገርላቸው ናቸው። (ኢዛ)



