ከ647 ቀናት እስር በኋላ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ይቀላቀላሉ

W/t Birutkan MidekssaEthiopia Zare (ማክሰኞ መስከረም 25 ቀን 2003 ዓ.ም. October 5, 2010)፦ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር የሆኑት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ነገ ጠዋት ረቡዕ መስከረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም. (ኦክቶበር 6 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) እንደሚፈቱ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለፁ። ለመፈታቱ ምክንያት የሽማግሌዎቹ ቡድን እጅ እንዳለበት ታውቋል።

 

በፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅ የሚመራው የሽማግሌዎች ቡድን በተለይም በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እና በወ/ት ብርቱካን መሃል በመግባት ሲያደራድር እንደነበር ምንጮቻችን ገልፀዋል። በዚህኛው ድርድር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የፈረሙት ወረቀት መኖሩን ገልፀዋል።

 

ለጊዜው የስምምነቱ ይዘት ምን እንደሆነ ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆኑት ምንጮቻችን፤ ምናልባትም ነገ ከወ/ት ብርቱካን መፈታት በኋላ በይፋ ሊገለጽ እንደሚችል ገልፀውልናል።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ጋር በመሆን ታህሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. (ዲሴምበር 29 ቀን 2008 እ.ኤ.አ.) ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ተኩል ላይ ቦሌ ከሚገኘውና ከሽማግሌዎቹ አንዱ የሆኑት ፓስተር ዳንኤል ከሚመሩት ”ፕሪዝነርስ ፌሎሺፕ” ጽ/ቤት ለአራት ሰዓታት ቆይተው ሲወጡ ወ/ት ብርቱካን ታስረው ሲወሰዱ፤ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ደግሞ ተደብድበው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው አይዘነጋም።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ረቡዕ የሚፈቱት ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ከስምንት ቀናት (በድምሩ ከ647 ቀናት) እስር በኋላ ሲሆን፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋርም ከረዥም ጊዜ በኋላ ይቀላቀላሉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከወላጅ እናታቸውና ከሕፃን ልጃቸው በስተቀር ማንም እንዳይጠይቃቸው ተከልክለው እንደነበር ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ