የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በኮሮና ተጠርጥረው ወደ ለይቶ ማቆያ ገቡ
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየሰፋ በመሔዱ ኬንያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ለይቶ ማቆያ እያዘጋጁ ይገኛሉ። በምስሉ ላይ የሚታየው በኬንያ ምጋቲ ሆስፒታል በለይቶ ማቆያ ልምምድ ሲደረግ የሚያሳይ ነው (ፎቶ፣ ሮይተርስ)
ኮሮና ቫይረስ ከተገኘበት ጃፓናዊ ጋር ተገናኝተው ነበር
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 15, 2020)፦ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ከተገኘበት ጃፓናዊ ጋር ተገናኝተው የነበሩት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ፤ በኮሮና ቫይረስ ሥጋት በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል።
ጃፓናዊው በትምህርት ዘርፍ በጎ አድራጎት የሚሠራ አባል ከመኾኑ ጋር ተያይዞ፤ የትምህርት ቢሮ ኃላፊውም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከጃፓናዊው ሰው ጋር በመገናኘታቸው ለብቻቸው ተለይተው እንዲቆዩና ሕክምና ክትትል እንደሚደረግላቸው ተገልጾላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ለብቻቸው ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
በጉዳዩ ላይ ከተሰራጩ መረጃዎች መረዳት እንደተቻለው ከጃፓናዊው ጋር ከተገናኙ አስር ቀናት ያለፋቸው ቢኾንም፤ እስካሁን እርሳቸው ላይ የተለየ ምልከት አልታየም። ኾኖም 14ቱን ቀን በለይቶ ማቆያ መቆየት ግድ በመኾኑ ይህንኑ እያደረጉ ነው። (ኢዛ)



