Ethiopian coffee ceremony. ቡና በጀበና እና በስኒጌቱ ኃይሉ

አቶ ዠ ከጸሐፌ-መፈክር ወደ ጸሐፌ-ተውኔት እሸጋግራለሁ ብለው መፈከራቸው እንዳለ ሆኖ፣ ይንን አስመልክቶም ለኢህአዴግ ፍቅር ቴአትር ቤት ሥራ አስቀማጭ ደብዳቤ መላካቸው እንዳለ ሆኖ፣ ... ከወራት በኋላ የአቶ ዠ ባለቤት ወይዘሮ ዘ ቡና አፍልተው ከአቦል እስከ በረካ ተጠጥቶ እንዳለቀና ሥኒ እያጠቡ እያለ ...

ወይዘሮ ዘ ገረሙህ? “ባልና ሚስት ካንድ ባህር ይቀዳል” ሲባል አልሰማህም? ባላቸው ዠ ከሆኑ እሳቸው ከ“ዘ” ሌላ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ዠ እኮ ባርኔጣ የደፋ ዘ ነው። ከምሬ ነው። ካላመንከኝ ሥለ ቃላትና ፊደላት የሚፈላሰፉ “ዲባቶ”ዎች ፈልግና ጠይቅ። ሥምህ ጨ ከሆነ የምታጫትና የምታገባት ኮረዳ ጠ ነው የምትባለው። እና ቡና ተጠጥቶ እንዳለቀ፣ አቶ ዠ ከባለቤታቸ ጋር “ጨዋታ” ጀመሩ።

”ጨዋታ”ው ሲያልቅ ጻፉት፤ አቶ ዠ፣ ጸሐፌ-ተውኔት። ገጸ-ባህርያት - ዠ እና ዘ ብለው ጀመሩ።

ዘ: እኔ የምልህ? ጠባብ ብሔርተኝነት ምንድነው?

ዠ: ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያልሆነ ማለት ነው?

ዘ: “ውሃ ሲወቅጡት እምቦጭ አለ” አሉ። ልዩነቱ ምንድነው?

ዠ: ጠባብ ብሔርተኝነትማ ልክ እንደምታጥቢው ሥኒ ማለት ነው።(አሉ አቶ ዠ የሚታጠበውን ሥኒ እያዩ።)ሥኒ ውስጥ ከጀበና ቡና ብትቀጂበት ያው ያቺኑ የተቀዳችውን ብቻ ነው የሚይዘው። ከዚያ በላይ አይችልም። ጠባብ ነዋ! በተፈጥሮው፣ ባሠራሩ ጠባብ ነዋ! ያ እንግዲህ የጠባብ ብሔርተኝነት ምሳሌ ሊሆን ይችላል።

ዘ: አሃ! (የገባቸው አይመስሉም፣ ወ/ሮ ዘ)

ዠ: ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ደግሞ እንደ ጀበናሽ ነው። የያዘውን ሁሉ የሚያከፋፍል። አየሽ ጀበና ታጋሽና ለጋሽ ነው። እሳት ላይ በዝምታ ተጥዶ፣ ቡና ተፈልቶበት፣ ያን ሁሉ ችሎ፣ በኋላ ለሥኒዎች ሁሉ የያዘውን ያከፋፍላል።

ዘ: አሃ!ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንደ ጀበና ነው? ከሰል ላይ እንደምጥደው ጀበና ነው? እሳት ጠግቦ ግንፍል ግንፍል እንደሚለው ጀበናዬ ነው?

ዠ: ኤዲያ! ያንቺ ነገር፣ ቢገነፍል ባይገነፍል የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መብቱ ነው።

ዘ: እንግዲህ ቡናዬን በሰላም ለመጠጣት፣ ግንፍል ግንፍል ባዩን ጀበናዬን፣ ከፊሉን ቡናዬን አፍሳሹን ጀበናዬን፣ በዚህም ምክንያት ከሰሌን የሚያዳፍነውን ጀበናዬን፣ ከከሰል አውርጄው እስኪሰክን በዝምታ መጠበቅ ያለብኝ ጀበናዬ ነው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ምሳሌ ነው የምትለኝ?

ዠ: እንዴ ይሄን ሁሉ ዓመት ታግሰሽ ኖረሽ የለም እንዴ? ”ግንፍል፣ ግንፍል የሚለውን፣ ሁሌ እሲሰክን መጠበቅ ያለብኝን” ብለሽ የምትታዘቢው?

ዘ: ህምምምምም ... እሱስ ልክ ነው። ታግሼ ችየዋለው። ሲሟሽ፣ ሲሟሽ ከከረመ፣ ከዛሬ ነገ ይሻለዋል ብዬ ችየዋለሁ። (ጀበና ትተው የወሬ ርዕስ ቀየሩ፣ ወ/ሮ ዘ) እኔ የምለው? ምሥር ደግሞ “ኢትዮጵያን እወራለሁ፣ አባይ ይነካና ዋ!” ብላ ትፎክራለች አሉ። እኔ እንኳን ጭምጭምታ ነው የሰማሁት። እሳት ላይ ተወርቷል አሉ። “ይቼ ጥሬ፣ ይቺ ምሥር፣ ካደረች አትቆረጠምም” አሉ አበው።

ዠ: ዛሬ ደግሞ ከበደ ሚካኤልን መሆን አማረሽ እንዴ?ምነው ተረትና ምሳሌ አበዛሽ?። ግብጽ በማለት ፈንታ ምሥር የምትይውና የምትተርቺው? ደግሞ የእሳት ወሬ አታምጭብኝ። እሳት ማለቴ “ኢሳት ይፋጃል“ ሲባል አልሰማሽም? ሲፈጃቸው እኔ ዠ የእሳቱ ማብረጃ፣ ማጥፊያ መሆን አልፈልግም። ”ግብጽ ብትመጣ እንዘምታለና! ግብጽ ምናባቷ እንዳትሆን ነው? እስኪ ትምጣና እናያለና!“ ነው የሚባለው።

ዘ: ፉከራ! መፈከር ብቻ!

ዠ: መፈከር ሥራዬ እንደነበር አጣሽው እንዴ?

ዘ: ዘመቻ? ዘመቻ? የምንበላው የሌለን ሰዎች በባዶ ሆዳችን ነው የምንዘምተው? አሃ!

(አሉ ወ/ሮ ዘ ወደሰማይ አንጋጠው፣ መንግሥተ ሰማያት ተከፍቶ የሆነ ነገር የነገራቸው መስለው ተናገሩ።)

አሃ! ስኳር! ስኳር ፋብሪካ ይስፋፋ የተባለው ለዚህ ነው ለካ! ስኳር እየበላን እንዘምታለና። ኢሃዴግ ስኳር እየቃመ ተዋግቶ አይደለም እንዴ ነጻ ያወጣን? ከተመክሮ የተገኘ መላ ነው። የስኳር ፋብሪካ ይስፋፋ!

(አቶ ዠ ለመናገር አፋቸውን ከፈቱ። ልክ ያኔ ...)

ዠ: ደግሞ ይህንን ግንፍል፣ ግንፍል ባይ፣ ገሚሱን ቡናዬን ደፊ ጀበና ከዛሬ ጀምሮ አልፈልግም ብለው ጀበናውን ወለሉ ላይ ከሰከሱት።

አቶ ዠ ይህንን “ጨዋታ” ጻፉና ወረቀቱን ኪሳቸው ውስጥ ከተው ወደ ኢህአዴግ ፍቅር ቴአትር ቤት አቀኑ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ