(አጭር ልብወለድ)

 ወለላዬ ከስዊድን

እግሬ እንደተነፋች ዶሮ ጢል ብሎ አብጧል። ጫማዬን ወጥሮት ማቆም እያቃተኝ ነው። ይኼን አሳዛኝ ሁኔታ ኃላፊው ማወቅ አለበት። ሄድኹኝ ምንም ሳልናገር ጫማዬን አውልቄ አሳየሁት። እሱም ምንም ሳይናገር ወደ ጓዳ ገብቶ ተመለሰ። የፕላስቲክ ነጠላ ጫማ አንጠልጥሏል።

ጥርስ ያልነቀለበት

እትብቱ ዘመዱ ያልተቀበረበት

ባዕድ መሬት ባዕድ

ዓይኑ ውሃ ኹኖ ቦታው ጭጋግ ለብሶ 

ባሳብ እየዋኘ ሄደ ተመልሶ 

አገሩ ናፈቀው 

አሁን ይህን ጊዜ ዓደይ አበባ ነው

ደማቅ ሰማያዊ ወሩ መስከረም ነው

አጭር ነበር ጉዞው የሄደው ባሳቡ

ወዲያው ተመለሰ 

ተመለሰ 

ዓይኑ እምባ አቀረረ። 

(ግጥም ገብረክርስቶስ ደስታ)

ስደት ከወጣሁ ሦስት ወራት አልፎኛል። በቀጥታ የገባሁት ወንድሜ ቤት ነበር። ሚስትና ሁለት ህጻናት ልጆች አሉት። ሆኖም የራሴ የሆነ አንድ መኝታ ክፍል አላጣሁም። ተዋበ በፊት የማውቀውን አይነት ሆኖ አላገኘሁትም። ሳቁ ደርቋል፣ አጫጭር ነገሮች ተናጋሪ ሆኗል። ነገሮች የሰለቹት አይነት ነው። ሊያውራ የጀመረውን እንኳን አይጨርሰውም። በእንጥልጥል እያለ ወደሌላ ይሸጋገራል። የሌላን ሰው ንግግር የሚሰማው ከፊሉን ነው። የገባው ስለሚመስለው አይፈልገውም፤ የአስራ ሁለት ዓመት የውጪ ቆይታው ብዙ ለውጦታል።

አመሉ ባይገባኝም አብረን መኖር ጀምረናል። ሚስቱ የሚገባኝን አክብሮት አልነፈገችኝም። ብዙ ጊዜ መንፈሣዊ መዝሙር ታዳምጣለች። ስለኖረችበት አካባቢና ስለቤተክርስቲያን ማውራት ያስደስታታል። በጨዋታ ማኻል በነገር ነደፍ ማድረግ ትወዳለች። ያም ሆኖ ብዙ የምታውከኝ ሴት አልነበረችም።

እነሱጋ በገባሁ ሦስተኛ ወር ተዋበ ሥራ አገኘልኝ። አያይዦ ምክሩን ያዥጎደጉደው ጀመር። “ስማ ማንንም ማመን አይገባህም። ሰው አገኘሁ ብለህ የልብህን ሁሉ አትዘርግፍ። የሥራ ሰዓትህን አክብር። ቀድመህ ግባ፣ ስትወጣም ሰዓቱን ጠብቀህ ውጣ። መጠጥ የሚባል አካባቢ እንዳትደርስ እዛ የጋፍከው ይበቃሀል …

በጥሞና አዳመጥኩት። አጉል እንደ አባት፣ እንደ አባት የሚያደርገው ቢያናድደኝም ከማድመጥ ውጪ ዕድል አልነበረኝም፣ ምክሩን አቋርጦ ሲያየኝ ከቆየ በኋላ “ተግባባን!?” አለኝ። “አዎን! ተግባብተናል፤ ግን የቋንቋውን ነገር እንዴት አደርጋለሁ? ማለቴ ሥራ ላይ …

“ስለቋንቋው አታስብ እያደር ትለምዳለህ። አንዳንድ የምትሰማቸውን ቃላቶች ለመያዝ ሞክር። ደግሞም በሥራው ጎበዝ ከሆክና ከሠራኽላቸው ስለቋንቋህ አይጨነቁም፣ በንግሊዘኛም መግባባት ትችላለህ።” በማግስቱ ወስዶ አገናኘኝ። ሥራው ላውንደሪ ውስጥ ነው። የሆቴሎችና የመሰል ድርጅቶች አንሶላ፣ ፎጣ፣ ብርድ ልብስ፣ ትራስ ልብስ፣ እና የመሳሰሉት ይታጠባሉ። የከተማው ልብስ ሁሉ የመጣ ይመስል፣ ቤቱ በልብስ ተጨናንቋል።

አሰሪው ወዲያውኑ እንደደረስኩ ከአንድ ሰው ጋር አቆራኝቶ ሥራውን አስጀመረኝ። የታጠበ አንሶላ ከጋሪ ላይ እያነሱ ጠረጴዛ ላይ መዘረር ያዝን። አንድ ጋሪ ጨረስን፣ ሌላ ተተካ፤ ያ ሲያልቅ ሌላ ቀጠለ፤ አንሶላውን ስንጨርስ ፎጣ ቀጠለ፤ ፎጣ ሲያልቅ ብርድ ልብሶች ታጥበው መጡ። ትራስ ልብስ ሌላም ሌላም የማያልቅ ሥራ፣ እየተጨመረ የሚሄድ ሙቀት ነፍሴ በአፍንጫዬ ልትወጣ ምንም አልቀራት። የተጠንጠለጠለውን የግርግዳ ሰዓት አየሁት፣ የፈጣሪ ያለህ ገና ለመውጣት ሙሉ ሰባት ሰዓት ይቀረኛል። አልጋ ላይ ተኝቶ ሞቱን እንደሚጠባበቅ በሽተኛ በፍራቻ ተዋጥኹ። አብሮኝ የሚሠራው በከፍተኛ ድምጽ አንባረቀብኝ። ሌላ እያሰብኩ ሥራው ላይ እንደደከምኩ የገባኝ በኋላ ነው።

እንደገና አንሶላ ተጀምሯል። ይበልጥ እየተጣደፍን መሥራት ጀመርን። ኾኖም አሰሪው አልረካብኝም፤ ወደኔ ሲንደረደር መጣ።

“እንግሊዝኛ ትችላለህ?”

“አዎን!” ተቅለሰለስኩ።

“በፍጥነት መሥራት ይገባሃል።” ከኔ አጣማጅ ጋር በሚያስደነግጥ ፍጥነት አንሶላውን እየዘረጋ አሳየኝ። ወይ ጣጣዬ እንዴት አድርጌ ነው እንደዚህ የምሠራው። በላብ በተጨማለቀው ፌቴ ላይ እንባዬ ፈሰሰ። ማንም ልብ ያለው የለም። አሰሪው እኔን አያይዞ ወደሌሎቹ ተፈተለከ።

እየተጣደፍኩ በመሥራት ላይ ነኝ። እናቴ እፊቴ መጣች “ሰው እንዴት የተኛበትን ማንጠፍ ያቅተዋል? የበላኽበትንስ ብታነሳው ምናለ? ተው! ልጄ ግፍ ይሆንብኻል”። በደንብ! እናቴ፣ ይኼው ግፉን አገኘሁት … ይቅር በይኝ። ጉሮሮዬ ላይ አንድ ነገር መጥቶ ተወተፈ። እናቴ ገጽታዋ እንደጠቆረ ፊቷን አዞረችብኝ። “ብዬህ አልነበር …

አባቴ ተራውን መጣ ነጭ ሸሚዝ ለብሷል። “ስማ አንተ! ይሄን ሸሚዝህን ብታጥበው ምናለ። ካልሲህን አውልቀህ በየስርቻው የምትወትፈው ህጻን ልጅ መሆንህ ነው? ብቻ መጨረሻህን አይቼ …”፤ አባቴ ይኼው መጨረሻዬ ይቅር በለኝ። ድምጼን ከፍ አድርጌ ይቀር በለኝ ስል ተሰማሁ። አብሮኝ የሚሠራው የተቆጣሁ መስሎት ሲያየኝ ከቆየ በኋላ ወደ አሰሪው ሄደ።

አሰሪው ወደኔ ሲመጣ ጊዜ አልፈጀበትም። እጄን ይዞ እየመራ ወደሌላ ቦታ ወሰደኝ። ፎጣ ለየብቻ የሚታጠፍበት ቦታ ነው። በትልቅ የፕላስቲክ ሙሉ ጢም ያለ የደረቀ ፎጣ ቀርቧል። የተለያዩ መጠን ያላቸው ፎጣዎች በአራት አይነት መልክ ይታጠፋሉ። በፍጥነት አስተጣጠፉን አሳይቶኝ ሄደ።

ማጠፍ ጀመርኩ ፍጥነት ቢያንሰኝም ሥራው ቀሎኛል። የቀረበልኝን አገባደድኹ ስል ሌላ ቀጠለ፣ እሱን ስጨርስ ሌላ፣ አሁን አቅለሸለሸኝ። ገና ሁለት ሰዓት ይቀረኛል። መቼ ነው የሚያልቅ? ምን አይነት ጉድ ውስጥ ነው የገባሁት? ተዋበ ፌቴ መጥቶ ተወዘፈ። ዛር ያስውበውና እዚህ አምጥቶ የሚጫወትብኝ እሱ ነው። ይሄ ሥራ ኾነና ደሞ ምክሩ በዚህ ላይ “አንተ ደግሞ ሠርተህ ጌድዮንን ታመጣለህ” ይበለኝ?! በስመአብ! …

እግሬ እንደተነፋች ዶሮ ጢል ብሎ አብጧል። ጫማዬን ወጥሮት ማቆም እያቃተኝ ነው። ይኼን አሳዛኝ ሁኔታ ኃላፊው ማወቅ አለበት። ሄድኹኝ ምንም ሳልናገር ጫማዬን አውልቄ አሳየሁት። እሱም ምንም ሳይናገር ወደ ጓዳ ገብቶ ተመለሰ። የፕላስቲክ ነጠላ ጫማ አንጠልጥሏል።

“ምንድነው?”

“ይሄን ቀይረህ ሥራ። ጊዜ አታባክን!”፤ አቋርጨ በመምጣቴ ተበሳጭቷል።

“አልሠራም! እግሬ እንደዚህ ሆኖ አልሠራም።” የራሴ ድምጽ ለራሴው አስደነገጠኝ። ጩኸትና ንዴት የተቀላቀለበት ነበር።

“መሄድ ትችላላህ። አያይዞም ነገም መምጣት አያስፈልግኽም። ለሥራው ብቁ አይደለህም” አለኝ።

* * *

እቤት ስደርስ ተዋበ በሁለት ልጆቹ ተከቦ ሶፋው ላይ ተጎልቷል። ባለቤቱ ማብሰያ ቤት ሳህን በማጣጠብ ላይ ናት። “ጌታው ደህና መጣህ?”

“ምን ጌታው ትለኛለኽ? ባርያው በለኝ” በንዴት መልስ ሰጠኹ።

“ምን ኾነሃል?”

“ምን ኾነሃል ትለኛለህ እንዴ ደግሞ? እየው እስቲ፣ ጫማዬን ወርውሬ እንደፊኛ የተነፋ እግሬን ዓይኑ ስር አስጠጋሁለት። “እየው ይኼን ደግሞ” ሁለተኛውን እግሬን ስቀይር ባለቤቱ መጥታ ነበር። ንዴቴንና ሁኔታዬን ስታይ ክው ብላ ቀረች። ልጆቹ ማልቀስ ጀመሩ። አባታቸውን የምደበድበው ሳይመስላቸው አልቀረም። እናትየው ልጆቹን እያባበለች ወደ መኝታ ቤት ገባች።

ተዋበ የሚናገረው አልነበረውም። የበላይነት ስሜቱ ሲተነፍስ ተመለከትኩ። ኩምሽሽ ብሎ አንገቱን ደፋ አላሳዘነኝም በለው በለው ነበር ያለኝ። ከላይ የለ ከታች የለ ጸጥ እንዳለ ቀረ። እኔ ቀጠልኩ። “ስማ እዚህ ያመጣኸኝ ለባርነት ነው እንዴ? እምበላው አጣሁ አላልኩህም። አሁንም እዚህ አገር በእንዲህ አይነት ኑሮ ህይወቴን ልገፋ አልፈልግም። እዛ ስትመጡ ሰው እየመስላችሁ፣ ጉራችሁን ትነፋላችሁ፤ እዚህ ሲመጣ ባዶ … እኔ እንደውም ድሮ የማውቅህ ተዋበ መሆንህንም እጠራጠራለሁ፣ አንተ ብሎ ተዋበ?! “ጀዘበ” ቢሉህ ይሻል ነበር። እንደጉድ ተንጣጣሁ። ተዋበ ባላሰበው ጊዜ እንደዚህ ባወረድኩት መአት ግራ ተጋብቷል።” ቃል ቢመልስ የበለጠ እንደምቀጥል ገብቶታል፤ ዝም በቃ ዝም …

ሶፋው ላይ እንደተዘረጋሁ እንቅልፍ ወስዶኝ ኖሮ እኩለ ሌሊት ላይ ነቃሁ። ጸጥ ያለ ሌሊት። ጠረጴዛው ላይ ምግብ ተከድኖ ተቀምጧል። ቀስ ብዬ ተነሳሁ እግሬ አሁንም እንዳበጠ ነው። ስነካው ቦታው ስርጉድ ብሎ ቀረ። ስራመድበት እያመመኝ መኝታ ቤት ገብቼ ተጠቀለልኩ።

ጠዋት ስነሳ እረፋዱን አምስት ሰዓት ሆኗል። አቤት! እንዴት ተኝቼ ኖሯል! ምን ተኝቼ ሞቼ ነበር ቢባል ይቀላል። ቤቱ ውስጥ ማንም የለም። ባልና ሚስት ሥራውን ሊሸከሽኩት ሄደዋል። ልጆቹን ከመዋያ ቦታቸው ሲመለሱ እንደሚያመጧቸው አውቃለሁ። እግሬን አየሁት በመጠኑ ጎደል ብሏል።

የማታው ነገር ሳስበው እፍረት ተሰማኝ። የኔ ልፍለፋ፣ የተዋበ ዝምታ፣ የልጆቹ ለቅሶ፣ የሚስቱ ልጆቹን ሰብስቦ መግባት፣ አሳፋሪ ነበር። እፍረት ቢሰማኝም እራሴን ጥፋተኛ ማድረግ አልፈለኩም። ነገሩን ለመርሳት ሞከርኩ ሆኖም ማታ መገናኘት ይኖራል፤ ምን ብዬ ነው ዓይናቸውን የማይ? የራሱ ጉዳይ የመጣው ይምጣ! ረሃብ አፉን ከፍቶ እያላመጠኝ ነው። ማታ የተቀመጠልኝን ምግብ ጥርግ አድርጌ በልቼ ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ።

ውጪው ደስ ይላል። ሙቀቱ ኃይለኛ ቢሆንም ከባህሩ የሚነፍሰው ነፋስ አቀዝቅዞታል። ቀዝቃዛውን ንፋስ እየሰነጠኹ ወደባህሩ ተጓዝኩ። መንገድ ላይ የፈረንጅ ባልና ሚስቶች አየሁ። ልጃቸውን በጋሪ አድርገው ይጓዛሉ። ባል ጋሪውን ይገፋል። ቦርሳ አንጠልጥሏል። በሌላ እጁ ትንሽ ሴት ልጅ ይዟል። ሚስት ፊት ለፊት ትሄዳለች ከነሱ ጋር ጉዳይ ያላትም አትመስል። ሰውዬው እመቤቱን የሚከተል እንጂ ከሚስቱ ጋር የሚሄድ አይመስል። አይ! ቁመናዋ ቀጥ ያለ አቋም ሁሉም ሴቶች እንዲሁ ናቸው። ወንዶቹ ናቸው የሚያሳዝኑ በካኒተራና በጅንስ ሱሪ ተጣብቀው ሲጎተቱ ነው የሚውሉት።

ሁሉም ወንድ መጀዘቡን ያየሁት ዛሬ ነው። ሚስቶቻቸው ሳይገርፏቸው አይቀሩም። ተዋበንም ሚስቱ ስትገርፈው ታየኝ። “በናትሽ! በናትሽ! …” ተንበርክኮ ይለምናል።

“ለምን ዕቃውን አላጠብክም?”

“ቸኩዬ ወጥቼ ነው”

“በሁሉም ነገር ነው የሰነፍከው …”

“ሥራው እያደከመኝ ነው።” … ራሴው በፈጠርኩት ምናባዊ ቀልድ በሳቅ ፈረስኩ። ብዙ የጀዘቡ ባሎችን እያሰብኩ ወደ ባህሩ ተጠጋሁ። ባህሩ ግራና ቀኙን በትላልቅ ሆቴሎች ተከቧል። አሸዋማ ሜዳው ላይ በስስ የውስጥ ሱሪና በጡት መያዥያ ብቻ ያሉ ብዙ ሰዎች በላስቲክ አልጋ ፀሐዩ ላይ ተዘርረዋል። ቀርቤ በማየት ላይ ነኝ። በደረታቸው የተኙ ረጃጅም ቀጫጭን ሴቶች፣ ሌሎች ሰፊ የፀሐይ መነጽር ያደረጉ በጀርባቸው የተኙ ሴቶች፣ ቀይ፣ ቢጫ፣ ሰማያዊ፣ ግራጫ፣ ዥንጉርጉር፣ የተለያየ የውስጥ ሱሪ “ስብዐት ለአብ! ምን ይመስላሉ?” ፊት ለፊት ያለው ደረጃ ላይ ተቀመጥኩ። በቅርብ አፍጥጨ እያየሁ ነኝ። ብዙ ግን አልቆየሁም ተነሳሁ። ሁልግዜ እንደዚህ ሆነው ሳያቸው ያመኛል። ምን አስደበቀኝ ህመም አይደለም እናደዳለሁ። ምን መናደድ ብቻ … እናታቸውን ብሽቆች ተነሳሁ፣ የባህሩ ጠርዝ ላይ በቀጭኑ በተዘረጋው መንገድ ቁልቁል መጓዝ ጀመርኩ። ብዙ ሰው ወደዚያ እየተጓዘ ነው ቁምጣ ያለበስኩ እኔ ብቻ ነኝ። ጅንስ ሱሪዬን ቆርጨ ቁምጣ አድርጌ ልለብሰው አስቤ ነበር፤ ግን ፈርቼ ተውኩት። ፈጥሮ ፈጥሮ ፈጣሪ የጡንቻ ስጋ የነሳን መሆናችን አናደደኝ።

እንደወትሮዬ ጥላ ቦታ ፈልጌ የባህሩን ትርዒት ማየት ያዝኩ። እነዛ ህመሞች ከሩቅ ይታያሉ። አሁን ግን ሰው ሳይሆን ሜዳ ላይ የፈሰሱ ፊኛዎች መስለዋል። ትናንሽ የሞተር ጀልባዎች ባህሩን እየሰነጠቁ ያልፋሉ። ትልቅ መርከብ በባህሩ ጥግ በኩል የሰመጠ ህንጻ መስሎ ተገሽሯል። መናፈሻው ላይ አልፈው አልፈው ከመሬት ተቸክለው በተሰሩት አግዳሚዎች ላይ ሴቶችና ወንዶች በጥንድ በጥንድ ተቀምጠዋል። አይስክሬም የሚልሱ፣ ከንፈር ለከንፈር የሚላላሱም አሉ።

ይሄን የመሳሰለው ነገር ባለፉት ሦስት ወራቶች በተደጋጋሚ ያየሁት ነው። ዛሬ ግን አንድ አዲስ ሁኔታ ተፈጠረ። ከቀኜ በኩል ባለው የባህር ጠርዝ አንድ ኢትዮጵያዊት እየመጣች ነው። በርግጥ ከሷም በፊት ሌሎች ኢትዮጵያውያን አይቻለሁ። አንዳንዶቹ አፍጠው እያዩኝ ሰላም ልላቸው ስል ፊታቸውን ያዞራሉ። የቁጣ ያህል ባንገታቸው ሰላምታ ሰጥተውኝ የሚያልፉም አሉ። ከሩቅ አይተው እንዳላየ የሚሄዱም ብዙ ናቸው። ያም ሆኖ አብዛኛዎቹን በዓይን አውቄአቸዋለኹ። የምትመጣዋ ሴት ግን አዲስ ናት። ከሴት ጋር ቁጭ ብዬ ያሳለፍኩት ጊዜ ዘመናት ያለፉት መስሎ ተሰማኝ። ድምጻቸው፣ ሳቃቸው፣ ኩርፊያቸው፣ ጠረናቸው እንደጉድ ናፍቆኛል።

ኢትዮጵያዊቷ እየቀረበችኝ መጣች። ስስ ሸሚዝና ከግሩ ሰብሰብ ያለ ቀላል ሱሪ ለብሳለች። ጠይም ሰልከክ ያለፊት፣ በግዴለሽነት የተያዘ ረጅም ጸጉር አላት። በላዩ ላይ ኮፍያ ደፍታለች። ደፍረስ ያሉ ዓይኖቿ ደስ ይላሉ። ከላይ ቀጥ ብሎ ወርዶ ማኽሉ ላይ ከፍ ያለው አፍንጫዋ ማንነቷን አክብዶት ስጋት ላይ ይጥላል። አቤት በራስ መተማመን እየተጀነነች ጎኔ ደረሰች። ብለክፋት ምን ታመጣለች? ምንም ይሄን ከማለቴ አፌ ቀደመኝ።

“ሄይ! ጠጅቱ ሰላም ነሽ?”

ፊቷን ወደኔ አዙራ አትኩራ ካየችኝ በኋላ “እኔን ነው?” አለች አፍንጫዋን ወደላይ እየፈነነችው።

“አዎን! ጠጅቱ አይደለሽ እንዴ?” ደንግጫለሁ የተሳሳትኩ ለመምሰል ጣርኩ። ድንጋጤዬን አውቃለች። ይበልጥ ተጠጋችኝ። ጆሮዬን ይዛ ሽቅብ ልታነሳኝ መሰለኝ። ወይ መዋረድ!

“ለመሆኑ የማናት ጠጅቱ?”

“አብረን የተማርን … ማለቴ የሰፈራችን ልጅ” ዕድሜዋን ስገምት ከኔ ጋር ልትማር የምትችል አይደለችም።

“ስማ! እዚህ ተቀምጠህ ጠጅቱ፣ ሻሽቱ እያልክ ሴት ከምትለክፍ ለምን ሥራ አትሠራም። አገር ቤት አደረከው እንዴ? የኛ አራዳ ባንተ ቤት መጠበሱ ነው። ስድ ካንተ የባስኩ ጨላጣ የመነን ተማሪ ነበርኩ”

“መንን!” አፌን ይዤ አያት ጀመር።

“አዎ! መነን፤ ምኑ ነው ያስገረመህ?”

“አይ የናቴን ስም ስትጠሪ ደንግጨ ነው።” ዋሸሁ።

“አትዋሽ! አሮጊት ናት ማለትህ ነው። ለማንኛውም ዕድሜዬንም ቢሆን ሰርቼበታለሁ።” እማታፈናፍን ሴት ሆነችብኝ። ይባስ ብላ ጎኔ ተቀምጣ በጥያቄ ታጣድፈኝ ጀመር።

”መቼ ነው የመጣኸው?”

“ሦስት ወራት አለፈኝ።” ፖሊስ የሚጠይቀኝ ይመስል ትክክለኛ ቃሌን በመስጠት ላይ ነኝ።

”ከየት ነው የመጣኸው?”

ኮስተር አልኩ “ከኢትዮጵያ ነዋ!”

”የአዲስ አበባ ልጅ ነህ?” አንገቴን ነቅንቄ አረጋገጥኩ።

”እኔም ያዲስ አበባ ልጅ ነኝ” ሳቅ አለች።

“ግን አትመስይም” ላበሽቃት ፈለኩ።

“እንዴት?”

“ሀርድ ትሰጫለሽ፣ ትቆጫለሽ፣ ምናምን አለ አይደል” … መሳቅ ጀመረች። ስትስቅ ደስ ትላለች። ያ ሁሉ ክብደቷ በኖ ጠፋ። የቤተሰብ ያህል የሚቀርቧት ሆና ተገኘች።

”ለመሆኑ ከመጣህ ሥራ ሠርተህ ታውቃለህ?”

“ሠርቼ ነበር”

”ታዲያ ለምን ተውከው?” ምንም አልተናገርኩ ጫማዬን አውልቄ እግሬን አሳየኋት።

”ምን ሆነህ ነው?” የትናንት ውሎዬን አንድም ሳላስቀር ነገርኳት፣ ከውስጤ አውጥቼ የጣልኩት ያህል ነበር ቀለል ያለኝ።

ቃል ሳትተነፍስ ካዳመጠችኝ በኋላ፣ ስለራሷ ማውራት ጀመች። እንደመጣች ሆቴል ተቀጥራ ትሠራ እንደነበር። ድስት ስታጥብ ኬሚካሉ የሁለት እጆቿን ቆዳ ቀፎ እንዳነሳው። አልጋ ማንጠፍ ጀምራ ወገቧን ሰባብሮ እንደጣላት። ሽማግሌና አሮጊቶችን መርዳት ተቀጥራ ሳይሆንላት እንደቀረ። የቢሮ ጽዳት ገብታ ያጋጠማትን አንድም ሳታስቀር ዘክዝካ ነገረችኝ። ይህን ስታወራ ዓይኖቿ በእንባ ረጥበው ነበር፤ የሚያስለቅሳት ግን ያ ብቻ አልነበረም፤ አያይዛ እንዲህ አለችኝ፤ “በዛው ወቅት እናቴ ሞተችብኝ፣ ችግሬን እማዋየው ኀዘኔን እማካፍለው ማንም አልነበረም፣ ባህር አጠገብ ብቻዬን እየሄድኩ አለቅስ ነበር።” እንባዋ እንደገና ፊቷን ሞላው። ምን ብዬ እንደማጽናናት ላውቅ አልቻልኩም፣ እንባዬ ግን ከሷ ባልተናነሰ ሁኔታ ይፈስ ጀመር። በራሴ ብሶት የፈሰሰው እንባዬ በልቧ ውስጥ ትልቅ ስፍራ መያዙን ያውኩት ግን በኋላ ነበር።

በዝምታ ባህሩ ላይ እንዳፈጠጥን ብዙ ቆየን። ከብዙ ዝምታ በኋላ፤ እዚህ ከተማ ነው የምትኖሪው? ብዬ በመጠየቅ ዝምታውን ገፈፍኩት።

“አይደለም! ከዚህ አራት ሰዓት የሚያስኬድ ቦታ ነው ያለሁት። ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር ለሦስት ቀናት እረፍት ነበር የመጣነው። እነሱ ክፍል ሲገቡ እኔ ባህሩን ለማየት መጣሁ። ነገ በጠዋት እንመለሳለን። ለመሆኑ እዚህ ዘመድ አለህ?”

“አዎን! ወንድሜ አለ”

”እሱጋ ነው ያረፍከው?”

“ሌላማ የት እገባለሁ ብለሽ?”

”ይሄውልህ እኛ ባለንበት ከተማ ባለቤቴ በበላይነት የሚመራው ድርጅት አለን። ድርጅቱን በቅርቡ ልናስፋፋው አስበናል። በዛን ጊዜ እኛጋ ሥራ የማግኘት ዕድል ይኖርኻል፣ ብዬ እገምታለሁ። ሥራውም ከነገርከኝ ሥራ መሻሉ አይቀርም። ወንድምህ ከዚህ በመራቅህ የሚከፋ አይመስለኝም። አንተስ ሥራው ቢገኝ መምጣት ትፈልጋለህ?” ብላ ጠየቀችኝ።

“እንዴ! ሥራ ተገኝቶ ነው! የትስ ቢሆን ምን ቸገረኝ። ልሠራ አይደል እንዴ የመጣሁት።” ቀልጠፍ ብዬ መልስ ሰጠሁ። ከትንሽ ቦርሳዋ ውስጥ ካርድ አውጥታ ሰጠችኝ። የድርጅቱ ስም አድራሻውና የስልክ ቁጥር ሰፍሮበታል፣ ከላይ ኤልሳበጥ ካሳዬ ጀነራል ማናጀር የሚል ስም በወርቃማ ቀለም ሰፍሯል። “በዚህ ስልክ ደውል፣ ማናት ቅድም ያልካት ጠጅቱ ነው ምናምን ሳልሆን ኤልሳቤጥ ካሳዬ ነኝ።” ትስቅ ጀመር።

የተቀጠርኩ ያህል ብድግ ብዬ ምስጋና አቀረብኩ። ለሷ ያለኝ አክብሮት ገና በፊት ሰማይ ጥግ ደርሶ ነበር። ለቅድሙ ለከፋ ግን ይቅርታ መጠየቅ አላስፈለገኝም። ”ምንም ችግር የለም ደውል የወንድምህንም ስልክ ብትሰጠኝ ጥሩ ነው አለች”። በብጣሽ ወረቀት ጽፌ ለመስጠት አፍታም አልወሰደብኝ። ልትሄድ ተነሳች፤ ያረፉበት ሆቴል መግቢያ ድረስ አብረን ተጓዝን። ልንለያይ ስንል “ምናልባት በሌላ ጉዳይ ከመጣሁ ባህሩን ድጋሚ ልንጎበኘው እንችላለን” አለችኝ።

“አይ! ባህሩጋ ካንቺ ጋር መሂድ አልፈልግም።”

”ለምን? አለች በመገረም።

“ዳግመኛ አብሬሽ ማልቀስ ሳይከብደኝ አይቀርም” አልኳት። በሳቅ እየተንፈረፈረች ወደ ሆቴሉ ገባች። ካርዱን እንደገና አውጥቼ አየሁት። ”ኤልሳቤጥ ካሳዬ - ጀነራል ማናጀር”

* * *

የስደት እፍታ - ፋሲል አየር ወለድ

የትናንት ውሎዬንና የዛሬ ገጠመኘን እያሰብኩ ባህሩን ለቅቄ ወደ ከተማው አመራሁ። የሥራ ሰዓት መውጫ በመሆኑ የብዙ ሰዎች እንቅስቃሴ ይታያል። ደስ ደስ የሚሉ ቡና ቤቶች፣ ተደርድረዋል፤ መግባት አማረኝ ኪሴ ያለው ገንዘብ ለቢራ መጠጫ እንደማያንስ አውቃለሁ። ”ሀፒ ሀወር” የሚል የተጻፈበት ቤት ገባሁ። ወንበር አልያዝኩም በቀጥታ ባኮኒው አጠገብ ተጠጋሁ፣ ምን ምን የቢራ አይነት እንዳለ እስከዋጋው ግርግዳው ላይ ተለጥፏል። ረከስ ያለውን አዘዝኩ አብዛኛው የሚጠጣው እሱኑ ነበር። ባለጌው ወንበር ላይ ቂብ ብዬ የቀረበልኝን ድራፍት በአንድ ትንፋሽ አጋመስኩት።

ከመጠጥ መደርደሪያው ከፍ ብሎ በደንብ በተዘጋጀ ሁኔታ የብዙ ሰዎች ፎቶ በምርጥ ፍሬም ተሰቅሏል። ባለጢም፣ ባለፒፓ፣ ወፍራም ቀጭን፣ ወላቃ፣ የሚስቅ፣ የተኮሳተረ የተለያየ መልክ፣ የቴክስ ኮፍያ ያደረገም አለ። አንድ ደግሞ ፎቶ የሌለበት ምርጥ ፍሬም የመሃሉን ቦታ ይዟል። የሃገሩ ታላላቅ ሰዎች ይሆናሉ ብዬ ገመትኩ። ግምቴ ልክ መሆኑን ማረጋገጥ ግን ነበረብኝ። ድራፍቱን አጋብቼ ሁለተኛውን ሳስቀዳ እነዚህ ሰዎች ምንድናቸው? ብዬ ባለቤቱን ጠየኩ።

እንደቀልድ ዞር ብሎ አይቶአቸው ሲያበቃ ”የዚህ ቤት የረጅም ዘመን ምርጥ ጠጪዎች ነበሩ። ዛሬ ሁሉም ተለይተውናል …” እንዳለኝ በርከት ያሉ ሰዎች ስለገቡ ለመታዘዝ ወደነሱ ሄደ። ጎኔ ተቀምጦ መጽሔት ያገላብጥ የነበረው ሰው መጽሔቱን እፊቱ ወርውሮ ወደኔ ዞረ። መደቡ ጥቁር ሆኖ ቀይ መስመር ያለበት ሸሚዝ ለብሷል። እጅጌውን እላይ ድረስ ጠቅልሏል። ቴክስ ሽማግሌ ነው፤ በመጠኑ አይቶኝ ካጠናኝ በኋላ “ሁሉም የዚህ ቤት ደንበኞች ነበሩ። በየተራ አለቁ። ይታይኻል የሞቱበት ዓ.ም. ከስር ተጽፏል።” ያላየሁትን ነገር አሳየኝ። ከሞተ ሃምሳ ዓመት ያለፈው ሁሉ እንዳለ አቀናነስኩ።

ቀጠለ “እነዚህ ፎቷቸው የተገኘ ብቻ ናቸው። አንዳንድ ብኩኖች ደግሞ እነዛውልህ” አለኝ። ባመላከተኝ ጠርዝ ደግሞ ፒፓ፣ ብዕር፣ መነጽር፣ ሻርፕ፣ ላይተር እና ሌሎች እቃዎች በተመሳሳይ ምርጥ ፍሬም ተከተው ተሰቅለዋል። ከስራቸው በወርቅማ ቀለም ስማቸው ተጽፏል። ምንድነው? ለማለት ወደ ሰውዬው ዞርኩ፤ “ጥለው የሄዱት እቃ ነው፣ ሲሞቱ ውለታቸውን የማይረሳው የተከበረው ቡና ቤት እንደዚህ በክብር እንዲቀመጥላቸው ያደርጋል” አለኝ። ራሴን በመነቅነቅ አድናቆቴን ገለጽኩ።

ቴክሱ ማስረዳቱን አላቆመም፣ “ይሄ ክፍቱ ፍሬም ደግሞ መጠጥ እየጋቱ የሚያሰናብቱን ክቡር ሰብሳቢያችን ሲሞቱ ፎቷቸው የሚያርፍበት ቦታ ነው።” በሁለት እጁ ባለቤቱን አመላከተኝ። ጎናችን ያሉ ጨዋታውን የማይሰሙ የመሰሉ ሰዎች ሁሉ ከኔና ከሰውዬው ጋር ይስቁ ጀመር። ሰውዬው አላቆመም፤ “ከባዶው ፍሬም በላይ ያሉት ሦስት መኳንንት ደግሞ እኛን ላሁኑ ባለቤት አደራ ሰጥተው ያለፉ አባትና አያቶቹ ናቸው። ለውለታቸው ክብር ባርሜጣዬን አነሳለሁ።” ያክተር ሳቁን ለቤቱ ለቀቀ። በመጨረሻ ወደኔ ጠጋ ብሎ ሚስጢር እንደሚናገር፤ “ወደፊት እኔም ከነዚህ ክቡር ጓደኖቼ ጎን ቦታ አገኛለሁ የሚል እምነት አለኝ። ይሄንንኑ እምነቴን ለማጠናከር ነው ዛሬም እዚህ የተገኘሁት” ብሎኝ እየሳቀ ድራፍቱን አነሳ። ከዚህ በኋላ እሱ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሃገሩ ቋንቋ ወሬውን፤ እኔም የራሴን ሀሳብ እያመነዠኹ ቆየን። በኋላ ግን ወደኔ ዞሮ “ከዬት ሀገር ነው የመጣኸው?” አለኝ።

“ከኢትዮጵያ”

“ኦ! ከኃይለሥላሴ ሀገር ”

“ልክ ነው”

“ስመ ገናና መሪ ነበሩ። እዚህ አገር የመጡ ጊዜ በአካል አይቻቸዋለኹ። ያን ጊዜ ወጣት ነበርኩ። ለኃይለሥላሴ ክብር ለሁለታችን ቢራ ድገመን” ብሎ ለኔም አዘዘልኝ። ለኃይለሥላሴ ክብር አጋጭተን ተጎነጨን። ዛሬ የተዋበ ምክር አፈር አባቷ መብላቷ ነው። አሁን ወደ አራተኛ ድራፍት ተሸጋገርኩ። አፌ ሲፍታታ እየተሰማኝ ነው፣ ስለ ኃይለሥላሴ ሰፋ ያለ መግለጫ ሰጠሁ። ስለ ፊደላችን አወራሁ። ላሊበላና አክሱምም አልቀረኝ። ይሄንን የሚያውቁም የማያውቁም የጨዋታችን ተካፋይ ሆነው ቆዩ።

አሁን ቤቷ ሞቅ ብላለች፣ ሁሉም ሰው እያወራ ነው። አንዲት ሴት መጥታ ጎኔ ካለው ጠባብ ስፍራ ተውተፈች። ከሷና ከሰውዬው ማኻል በመሆኔ ትንሽ የመጨነቅ ስሜት ተሰማኝ። ሆኖም ደስታዬን አልነጠቀኝም። ሞቅታዬ ግን እየጨመረ ሄዷል። ምናልባት መጠጤን ንረት የሰጠው ሰውዬው ከድራፍቱ ጋር የጋበዘኝ ባለአጭሯ መለኪያ አልኮል ሳትሆን አትቀርም። ግን ጣፍጣኛለች። አቤት ከዛ በኋላ ድራፍቱ ደግሞ ሲጥም፣ ላላዬው ወስኜ የተውኩትን የግርግዳ ሰዓት ተመለከትኩት ከሌሊቱ አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል። የራሱ ጉዳይ! …

ሰውዬው እንደገና ጨዋታውን ከኔ ጋር አደረገ፤ ”ጌታው የት ሆቴል ነው የምትሠራው?” አለኝ ብዙ ማምሸቴ ሳይገርመው አልቀረም።

“የትኛውም ሆቴል አልሠራም”

”አሃ! ሌላ ሥራ ነው ያለህ ማለት ነው?”

“የለም! ጨርሶ ሥራ የለኝም።” ትንሽ ቆይቼ “ሥራ እየፈለኩ ነው።” የሚል አከልኩ። ሰውዬው ሲያስብ ከቆዬ በኋላ፣ ወደ ባለቤቱ እያመላከተኝ “እሱ አንዳንድ ጊዜ የሚረዳው ሰው ይቀጥራል። ምናልባት የሚፈልግ ከሆነ ብጠይቀው ምን ይመስልኻል” አለኝ።

“ጥሩ ሀሳብ ነው”።

ባለቤቱ ወደኛ ሲቀርብ “ይሄ ልጅ ሥራ ይፈልጋል። ምናልባት አንተጋ ይገኝ ይሆን” አለው።  

ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በኋላ ”አንድ አዲስ ሥራ ሊኖረኝ ይችላል” አለ።

“ምን አይነት ሥራ?”

ስለሥራው በሃገራቸው ቋንቋ ተናገረ።

ጠያቂው ይስቅ ጀመር። ሁሉንም ትሰማ የነበረችው ጎኔ የተቀመጠች ሴት ፈጣን በሆነ ሁኔታ መልስ ሰጠች። ንግግሯ ቁጣ ያዘለ ነበር። ሁሉም በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብቶ መናገር ጀመረ። የሚሉት ባይገባኝም መነሻው የኔ ሥራ ጉዳይ መሆኑ ገብቶኛል። ተጯጩኸው ተጯጩኸው ሲያበቁ አቆሙ። ይበልጥ ትቆጣ የነበረችው ሴትየዋ ነበረች።

ስለጉዳዩ ሰውዬውን ልጠይቅ ፈልኩ። “ምንድነው ያለህ ስለ ሥራው?”

”ፌዘኛ! ሰው ነው እባክህ፣ ለቁም ነገር የታደለ አይደለም አለኝ።”

“ለምን? ምን እንዳለህ አትነግረኝም?”

ወደኔ ጠጋ ብሎ ”እነዚያን የሟቾቹን ፎቶግራፎች ከተማውን በማዞር እያናፈስክ እንድትመልሳቸው ይፈልጋል። በቁማቸው መዝናናት የለመዱ በመሆናቸው ሰቅዬ ማስቀመጡ ግፍ ይሆንብኛል ነበር ያለው፣ ነገር ግን ቀልዱን ብዙዎቹ አልወደዱለትም” አለኝ። ንዴቴን ሳቄ አሸንፎት መሳቅ ጀመርኩ። እሱም ከቅድሙ ይልቅ አሁን ይበልጥ ይስቅ ጀመር። ከዚህ በኋላ ግን ብዙ መቆየት አላስፈለገኝም። መሄድ አለብኝ። እፊቴ ያለውን ድራፍ በአንድ ትንፍሽ ጨልጨ ሰውዬውን ተሰናብቼ ወደበሩ አመራሁ።

አቤት! ደስ ሲል፣ ሁሉ ነገር ደስ ደስ አለኝ። ያሉትን ሰዎች ሁሉ ወደድኳቸው። እየሳምኩ ልሰናበታቸው ሁሉ ፈለኩ። ፈገግታዬ ሞቋል። ይቺ ደስ የምትል አጋጣሚ ማለፍ የለባትም፣ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ። ምንም ነገር ለማድረግ ኃይሉም ችሎታውም ባሁኑ ሰዓት በጄ ነው። እናስ? ምን? መተላለፍያው ላይ ቆም ብዬ አሰብኩ። ምንም! በቃ! ምንም ሊመጣልኝ አልቻለም። ምንም ለማድረግ አለመቻሌን ሳስበው ወደ ብስጭት አመራሁ። እንደገና ደግሞ ዝፈን ዝፈን የሚል ስሜት ተሰማኝ፤ ምን ብዬ እዘፍናለሁ? የማይሆነውን፣ ወጥቼ የማደርገውን አደርጋለው ብዬ በቆሙት ሰዎች ማኻል እየተጋፋሁ ወደመውጫው ስቃረብ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ክብ ሰርተው ቢራ ሲጠጡ አየሁ።

“ሰላም ለናንተ ይሁን! ወንድሞቼ።” ቀኝ እጄን እንደሚባርክ አባት ወደ ላይ ዘረጋሁ።

“ሰላም ላንተም ይሁን!” ሞቅ ያለ አፀፋ ነበር የተሰጠኝ። ሞቅታ ደጉ ሁሉንም በየተራ እየጨበጥኹ፤ ስሜን አስተዋወቅኹ። የመጨረሻው ተጨባጭ እጄን ጠበቅ አድርጎ ይዞ፤ “እማውቅኽ አይመስለኝም፤ እዚህ ከተማ ነህ እንዴ?” አለኝ። አዲስ ነው ለማለት ተቸግሯል።

“አይደለሁም”

“ታዲያ ከየት መጣኽ?”

አናዳጅ ጥያቄ ነበር፤ ግን አልተናደድኹም። ወደ ጣሪያው አሳየኋቸው። ሁሉም ሽቅብ ተመለከቱ። “በዛ በኩል፣ ከሁለት ሰዓት በፊት በቀጥታ እዚህ ቤት ወረድኩ።” አልኳቸው፤ በጣም ሳቁ። ይቺ ንግግሬ ግን ”ፋሲል አየር ወለድ” የሚል ስም አትርፋልኝ እስከዛሬ መጠሪያዬ ሆናለች። ቢራ ጋብዘውኝ አብረን መጨዋወት ጀመርን። የኩምክና ወሬ እያወራሁላቸው፣ እየሳቅን፣ እየጠጣን፣ አመሸን። ከሆነ ሰዓት በኋላ ግን ያለውን አላወራውም። ላውራውም ብል አላውቀውም። በመጨረሻው ትዝ የሚለኝ ቢኖር አንድ ሰው ቤቴ በራፍ ድረስ እንደሸኘኝ ብቻ ነው።

* * *

ይህ የሦስት ወር የስደት ቆይታና የሁለት ቀናት ትዝታ ነው። እነሆ ይህ ከሆነ አስራ ስምንት ዓመታት አልፎታል። ዛሬ ነገሮች ሆኑ ተለውጠዋል። ተዋበ እዛው ቤት ከባለቤቱ ጋር ይኖራል። አሁንም አንደበተ ቁጥብና ጨዋ ነው። ልጆቹ ሥራ ይዘው ከቤት ወተዋል። አንዷ እዛው ከተማ ስትሆን፣ ሌላዋ ስፍራ ለውጣለች።

እኔ ከዛ ከተማ ወጣሁ። ኤልሳቤጥ ካሳዬ ቀጠረችኝ። ዛሬ ድርጅቱን በኃላፊነት ከሚያንቀሳቅሱት ሰዎች ማኻል አንዱ ነኝ። በሥራው ላይ ለአስራ አምስት ዓመታት ቆይቻለሁ። የኤልሳን እህት አግብቼ፣ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጆች አሉኝ። ባለቤቴ ገነት ካሳዬ ትባላለች፣ ውብና ሸጋ አመል ያላት ልጅ ናት።

ተዋበ እንዳለኝ ጌዲዮንን አምጥቼዋለሁ። ምን ጌዲዮን ብቻ ትንሿ እህታችንም እዚኹ ናት። ጌዲ እንደኔ አልከፋውም፣ ወዲያው ሥራ ያዘ። ቆይቶ ታክሲ ነጂ ሆነ። ወፍሯል፣ በጣም ወፍሯል። ስማ ጌዲዮን እንዲህ ወፍረህ የሞትክ እንደሆን አንተን የሚሸከም የለም። እዛው የሞትክበት ነው በስብሰህ የምትቀር እንለዋለን፣ ጌዲ መልስ አለችው፤ ለዚህ አትስጉ ልክ ልሞት ትንሽ ሲቀረኝ አዳሬን ጉድጓዱጋ አደርጋለሁ። መቼም ገፋ አድርጋችሁ መክተት አያቅታችሁም። ይስቃል ... አላገባም ብቻውን ቤት ይዞ ይኖራል።

ትንሿ እህታችን የኔ ቢጤ ቅብጥብጥ ሆነች። የውጪ ሀገር ኑሮን ልትለምደው አልቻለችም። እንደመጣች ያረፈችው ተዋበ ጋር ነበር። ሥራም አግኝታ ነበር። ከሁለት ወራት በላይ አልቆየችም ጥላ ወጣች።

”ለምን ተውሽው?”

”እኔ እንደዚህ ያለ ጥብስ ያለ ነገር አልፈልግም።” መልሷ እንዲሁ ነው ጥብስ ያለ ነገር። እኔጋ ቀየረች ከባለቤቴ ጋር አንድ ሰሞን ተወዳጁ። ጸጉር ይሠራሩ ነበር። አብረው ወጥተው አብረው ገቢ ነበሩ። ሥራም እኛ ድርጅት ያዘች። ዕድሜ ለኤልሳ እንኳን እህቴን አውቀዋለሁም ላልኩት አታሳፍረኝም፣ ”አላቃሽ ወንድሜ ...” ትለኛለች። ለሣራ የሚስማማ ሥራ ነበር የሰጠቻት፤ ተወችው እንደገና ጌድዮን ቤት ሄደች። ከጌድዎን ቤት ወጥታ ተዋበ ጋር ተመልሳለች። አዲስ ሥራም ጀምራለች፤ ሁሉን ነገር ጥብስ ያለ ስለምትል ስሟን ትተን ”ጥብስ” ካልናት ቆይተናል።

በአበሻ በዓላት ተዋበ ቤት የመሰብሰብ ልምድ አለን። በአንድ የበዓል ሰሞን ከጌድዮን ጋር እዛች ቢራ ቤት ሄድኩ። ቤቷ እንደነበረች ቆየችኝ። ወንበሮቹ እንኳን የድሮ ቦታቸውን አለቀቁም። ወደ ባንኮኒው አመራሁ። ከባኮኒው ጀርባ መጠጥ የሚቀዳው ሌላ ሰው ነው። ማንንም መጠየቅ አላስፈለገኝም ከሙታን ፎቶዎች ማኻል ክፍቱን ቦታ ተመለከትኩ የድሮው ባለቤት ቦታውን ይዞ ገጭ ብሏል። ያንን ወዳጄንም ፈለኩ፣ እሱ እንኳን አይሞትም አልኩኝ በሃሳቤ፤ ግን ልክ አልነበርኩም። ከወዲኛው ጠርዝ በኩል ያቺን ቀይ መስመር ያለባትን ሸሚዝ እንደለበሰ ፎቶው ተሰቅሎ አየኹ። ሚስኪን! አሳሳቁ አሁን ድረስ አይረሳኝም። እዛ ከተማ በቆየሁበት ተጨማሪ ጊዜያት በተደጋጋሚ አገኘው ነበር።

ከጌዲዮን ጋር ቢራችንን በመጠጣት ላይ ነን። የዛን ጊዜውን ውሎና ታሪክ እስከዚህ ቤት ድረስ የተፈጸመውን ነግሬው ሳበቃ ልንሄድ ተነሳን። አሁን ግን እንደ ያኔው ዝፈን ዝፈን የሚል ስሜት ሳይሆን፤ አልቅስ አልቅስ እያለኝ ነው፤ ግን አላለቀስኩም። የዘፈንና የለቅሶ ጊዜያቱ መቀያየር እየገረመኝ እመውጫው በር ላይ እንደደረስን ”ፋሲል አየር ወለድ” የሚል የጅምላ ድምጽ ቤቱን ነቀነቀው፤ ስብዐት ለአብ!!! እነዛ ኢትዮጵያውያን ዛሬም እዛው ነበሩ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ