ይድረስ ለልጀ ደባልቄ ቢተው

"አንድየ ያውቃል እናትህም ትሾምና ትሸለም ይሆናል፤ የሷ ጠሎትና ምህላ እንደሁ ለፈጣሪዋ የቀረበ ነው።"

ዘጌርሳም

ይድረስ ለምንወድህና ለምትናፍቀን ልጃችን ደባልቄ ቢተው፤

እንዴት ከረምክ ልጀ? እኛማ ባለፈው ስናወጋ እመጣለሁ ባልከን መሠረት መምጣትኽን እየተጠባበቅን እንዳለን፤ ለአንተ ምኑን እነግርሃለሁ፤ በአሁኑ ወቅት ወሬውን ከእኛ ቀድማችሁ ስለምትሰሙት አገሩ ሁሉ ታምሶ የመንግሥት አልጋም ተናውጦ በመክረሙ ያገርህ ገበሬ በነቂስ ሞፈርና ቀንበሩን ሰቅሎ፤ ቤት ያፈራውን መሣሪያ እየወለወለ ዱር ገብቷል። እኛ ግን አቅምና ጉልበታችን ቤት ስለዋለ ትመጣ ይሆናል በማለት በር በሩን እያየን በናፍቆትህ እንደተሰቃየን አለን፤ የሊቦው ጊዮርጊስ የተመሰገነ ይኹንና እስካሁን የደረሰብን አንዳችም ክፉ ነገር የለም። እናትህ ግን ክስት ጥቁር እንዳለች በየደብሩ እየዞረች ያልተሳለችበት ታቦትና ያልቋጠረችለት የስለት ገንዘብ አይገኝም። ሌትና ቀን ዓይንህን እንዲያሳያት ያን የምታውቀውን የሊቦ ጊዮርጊስን አቀበትና ቁልቁለት ደከመኝ ሳትል ስትወጣ ስትወርድ ከረመች፤ ምን እሱ በቅቷት! ጣራ ገዳምና ዘንግ ሚካኤል ድረስ ሳይቀር ትመላለሳለች።

አንድዬ እሱ ያለው አይቀርምና ከጧት ማታ ሳይታሰብ ነገሩ ሁሉ እንደ ክረምቱ ጊዜ የእርብ ውኃ ድፍርስርስ አለብን፤ ሕዝቡም ከሽማግሌ እስከ ኮበሌ በነቂስ በመንግሥት ላይ አምጦ ተነሳ። መንግሥት ተብየውም ለነገሩ ሲገባም አላማረበት ነበር፤ አሁን ደግሞ ሲወጣ የከፋ ዕጣ ክፍል ገጠመው፤ “ሲገባ ያልተቀበሉት ሲወጣ ሸኝ የለውም” ይባል የለ፤ ያለ ቀልብ ገብተው ቀልበ ቢስ ኾነው መውጣታቸውም እውን እየሆነ ነው። የድሮው መንግሥት ወድቆ አሁን በመጥፋት ላይ ያሉት ሲተኩ ወገንህ በሙሉ ከላይ እስከ ታች ተከፍቶና ሆደ ባሻ ሆኖ ስለነበር በግልጥና ጠባቂ በሌለው ኬላ ሰተት ብለው እንዲገቡ ፈቀደላቸው፤ ኸዚያማ ድፍን አገሩን ባለቤት አልባ አደረጉትና ለወሬ ነጋሪ እንዳይተርፍ አርገው ሀብትና ንብረቱን ቀምተው ጥሪት አልባ አርገውት ቆዩ፤ አፈር ገፊውም ከርስት ጉልቱ ተነቅሎ ሁሉም ወደ ከተማ ፈለሰ።

ኤዲያ! ኸዚያማ ምን ልበልህ ያልፍልኛል ብሎ ከተማ የገባው ሁሉ የሚልስ የሚቀምሰው የሌለው የበይ ተመልካች ሆኖ ኸረመ። ብሶቱ ውስጥ ለውስጥ አገናኝቶት ኑሮ ወንጭፍ እንደተወረወረበት የወፍ መንጋም በአንድ ላይ ግር ብሎ ተነሣ፤ ወጣቱ ወንድና ሴት ሳይለይ የኔ ቢጤ አዛውንቶች ሳይቀሩ እናቶችን ጨምሮ የአመጡ ተካፋዮች ኾኑ። በድሮው ጊዜ ሕዝብ ሲያምጥ ውስጥ ውስጡን ተሰማምቶ በነቂስ ያለውን መሣሪያ እየወለወለና ጀሌውም ዱላና ቆንጨራውን እየመዘዘ ጫካ ይገባ ነበር፤ ሴቶችም በምስጢር ስንቅ ያቀብላሉ፤ እንደዚህ ነበር የአባት አደሩ በመንግሥት ላይ ሲታመጥ። የአሁኑ የእናንተው ዘመን ደግሞ ፊት ለፊት እንደ ሻምላና ገና ጨዋታ ውረድ እንውረድ ተባብሎ ነው የሚሞሻለቀው።

የሕዝቡ አመጥም እንደ ውኃ ሙላት ነጎደ፤ እናማ የመንግሥት መሃያ ተቀባይ የሆነው ወታደሩ ከኪሱ ምንም ሳያወጣ በታጠቀው ነፍጥ ወገንህን በየቦታው ክፉኛ ፈጀው። በአንዳንድ ቦታማ ጥቃቱ የፈሪ ዱላ ዐይነት ነበር፤ ፎቅ ላይ በመውጣትና ቤት ውስጥ ተደብቀው በመስኮት እያነጣጠሩ ብዙ ሕዝብ ጨረሱ። ሕዝቡም ይኽን መሳይ የግፍ ጥቃትና ጭካኔ ሲያይ ሞቱን ተጠይፎ እየፎከረና እያቅራራ በጨበጣ ፍልሚያ የሞት ሽረቱን ተያያዘው። ባለ መሃያው ወታደርም ነገር ዓለሙ ከአቅሙ በላይ ሆነበት፣ አለቆቹም መሸሽና መደበቅ ጀመሩ። በየጎበዝ አለቃው የሚመራው አሻፈረኝ ባይነት የጋራ አለቃና አዋጊ እንዲኖረው አስፈለገው። ሦስት ብልህ የተባሉ ሰዎች ውስጥ ውስጡን መክረውና ዘክረው በመስማማት ብቅ አሉ፤ ሦስቱም ወደ ገደል በመንከባለል ላይ ካለው መንግሥት ጋር አብረው የሠሩና ውስጥ አዋቂዎች ናቸው ይባላል።

ኤዲያ! ኸዚያማ አንድ ቁመቱ የፋርጣውን ሽፍታ አመሸ ትርፌን የሚያክል ቆፍጣና ወጣት አለቃ ወጥቶ ሕዝቡን በማረጋጋት እኛን ተከተሉን አለ። በድሮ አለቆቹም ላይ ቂም ቋጥሮ ኖሮ ክፉኛ ዛተባቸው፣ ንቀቱንም በሕዝቡ ፊት ገለጠላቸው። ወገንህ በሙሉ ለአያሌ ዓመታት አጥቶትና ናፍቆት የነበረውን የአገርና የባንዲራ ፍቅሩን እንደ ቡናና ዕፀ ፋርስ ሱስ ነው ሲለው በደስታ ፈነደቀና ሞቴን ከአንተ ጋር ያርገው ብሎ ተማምሎ ሆ! ብሎ ተነሣ።

ሁለተኛውና የእርሱ ባልንጀራ የሆነው አለቃ ገንባሩን እንደ ነብር ፊት ኮስትሮና ቋጥሮ ብዙም ሳይናገር ሙያ በልብ ነው ያለ ይመስላል፤ እንደ ኮርማ በሬ እየተንጎራደደ በልበ ሙሉነት ተከታዩን አሰባስቦ ለድሮ አለቆቹ የጉሮሮ አጥንት ሆነባቸው።

ሦስተኛው አለቃ ግን እንኳንስ አንተ ጨቅላው እኔ ይህን ያህል ዘመን ፈጣሪየ የዕድሜ ባለጠጋ ሲያደርገኝ ያላየሁት አንደበተ ርዕቱና ንግግሩ እንደ ማር የሚጥም ትንሽና ትልቁን አክባሪ፣ ሴትና ወንዱንም በእኩል ዓይን የሚያይ፣ በአፍህ ማር ይዝነብ አስብሎ እረኛንና አዝማሪን ያዘፈነ እጡብ ድንቅ የሆነ አንጎሉ ክፍት ያለ ሰው ነው። የእሱን ንግግር ያዳመጡ የየአድባራቱ ቃለ እግዚአብሔር አስተማሪና ሰባኪ መምህራንና ቀሳውስትም እኛ አፍ የለንም፣ ምንስ አውቀን እንዲሉ አሰኝቷቸዋል። ያገሩንና የወገኖቹን ፍቅር ሲገልጥም፤ “እኛ ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ ነን” አለ። ወገንህም ከደስታው ብዛት በእንባ ተራጨ፤ እሱም በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ በፍቅር ጥቅልል ብሎ ተኛበት፣ በአገሩ ሕዝብም ተኩራራ።

ደባልቄ!

እንደ እኔ አባትህ እኮ የታደለ የለም። ብዙዎች ባልንጀሮቼ የዕድሜ ዘልዛላ አረከን እያሉ ፈጣሪያቸውን ሲያማርሩ፤ ለእኔ ግን አንተን ፈረንጅ አገር የላከልኝ ሳያንሰኝ፤ ይህን የዛሬውን ደስታ በአካል ቁሜ እንዳይ አብቅቶኛል። ሰውየው እኮ በዚህ ይብቃህ አልተባለም፤ ገና ዘውድ ጭኖ ንጉሥ ትኾናለህ የተባለለትና ትንቢት የተነገረለት ነው አሉ። እሱም ይኽን ያውቃል፣ ገና በሰባት ዓመቴ ለናቴ በራእይ ተገልጦላታል ብሎ በሕዝቡ ፊት በጠራራ ጠሐይ ተናግሮታል፤ “የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ፣ የሚያጠግብ ቂጣ ከምጣዱ” ይባል ይኽ አይደል። ለእኔም እኮ አንተ ኑሮህና ግንባርህ ፈረንጅ አገር እንደሚሆን ግልጥ አርጎ አሳይቶኝ ነበር፤ ግልጥ ያልሆነልኝ ነገር ቢኖር መተዳደሪያህን አልነገረኝም ። ይኹን አገር ባትገዛም የሚያይህ ስለሌለ “ሾላ በድፍኑ” እንደሚባለው ስለ አንተ ሳወጋ ግልጥልጥ ሳላደርግ ለአገርህ ሰው በሞላ ደግ ደጉን ብቻ እናገራለሁ፤ የኛ ሰው እንደኹ አገሩን የለቀቀ ሁሉ ደልቶትና ተመችቶት የሚኖር ነው የሚመስለው።

የጧት ግንባርህና እህል ውኃኽ እንዲኽ ፈረንጅ አገር ሊሆን ቻለ እንጅ፤ እንደኔና እንደ እናትህ ምኞትና ጠሎትማ ኸዚሁ አገርህ ላይ ተድረህና ተኩለህ፣ ወልደህ ከብደህ፣ ተከብረህና እኛንም አስከብረህ እንድትኖር ነበር። ገበሬ ኾኖ አርሶና አፍሶ መኖሩ ጌጥ ቢሆንም፤ ድካሙ ጭንቅ ስለሆነ ያኹኑ ኑሮህ ይሻላል። እንኳንም ከአፈር ገፊነት አመለጥኽ። ኸዚህ ያሉት ያንተ ባልንጀሮች አፈር ገፊ እንደኾኑ አፈር እየሆኑ ነው ያሉት፤ ለመሆኑማ ሁሉም አልቀዋል እኮ፣ ማንስ ተርፎ እከሌ ልበልህ …

ደባልቄ!

ወደ ጀመርነው የአገራችን ጉዳይ ልመልስህና አሁን መጨረሻ ላይ ደሞ አንድ ልባም የሆነ ቁመናው ዘለግ ብሎ ሰውነቱ ደልደል ያለ አራተኛ አለቃ ከሦስቱ ጋር ተዘንቋል። አሁን አራት ኹነዋል ማለት ነው። በጠንካራ የእርሻ በሬዎች ብናሸርፋቸው እኮ ሁለት ጥንድ ጥማድ ኾነዋል። ጠንካራ የእርሻ በሬ ያለው ገበሬ ምርቱ በረከት ያለው ነው፤ ማሳውንም አልሞ ነው የሚያርሰው።

አሁን እነዚህ አራት ጠንካራ አለቆች ሕዝቡን ተከተለን ብለው ኬላ ኬላ ቢያስይዙትና በአዝማች በአዝማች ቢያሰልፉት፤ አገሩን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያረጋጉታል ብለን ተስፋ ጥለንባቸዋል። ተባራሪ ሽፍታ ብቅ ጥልቅ ማለቱ ስለማይቀር በስማ በለው ልናጠፋቸውና ልንማርካቸው አይጨንቀንም።

ደባልቄ!

ይኽ በዲስኩር ጎበዝ ነው ያልኩህ አለቃ፣ ሁኔታው በመጥሐፍ ቅዱስ ላይ ስላለውና መምሬ ይባቤ ከቅዳሴ በሁዋላ አንድ ሰሞን ያስተማሩን ትዝ አለኝ። ሙሴ የሚባል ሰው ነበር፤ የዘመኑ ንጉሦች ሊያስገድሉት ሲሉ በሽሽት ላይ እንዳለ ፈጣሪው ተገለጠለትና ከአደጋ አድኖ እንዲሰብክና እንዲያስተምር እረኞችና የኔ ቢጤዎች ወደ አሉበት ላከው። እሱም ስለ ሰላምና ስለ ፍቅር እየሰበከ እያለ ተከታዮች አገኘ ብለውን ነበር። የአሁኑ የኛው ሰውም ነገራ ነገሩ ይኽን ይመስላል። ሕዝቡ በነቂስ ደግፎታል አሉ። ሦስቱ አለቆች ተመካክረው እሱን የነሱ ኹሉ አለቃና የጦሩ ፊታውራሪ እንዲኾን መርጠውታል። እናቶች በሙሉ ያንተን እናት ጨምሮ እየመረቁትና ጠሎት እያረጉለት ይገኛሉ፤ እሱም ይኽን ተረድቶ ይመስላል አያሌ እናቶችን ትልልቅ አለቃ አርጎ ሹሟቸዋል። አንድየ ያውቃል እናትህም ትሾምና ትሸለም ይሆናል፤ የሷ ጠሎትና ምህላ እንደሁ ለፈጣሪዋ የቀረበ ነው።

እሱም ምንም እንኳን አንተ ከኔ አብልጠህ ነገሩን ብታውቀውም፤ ፈረንጅ አገር ድረስ በመሄድ የተጣላውን አጎናብሶና አስማምቶ፣ የታሰረውን አስፈትቶ፣ ያኮረፈውን አለስልሶና አሳምኖ፣ ተከፋፍለው የነበሩ የቤተስኪያን አለቆችንም አግባብቶና ይቅር አባብሎ ወደ አገራቸው መልሷል ይሉታል። የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው ዓለም በቃኝ የኸረሙትን ሁሉ ተራ ሌባንና ሽፍታን ሳይቀር በነጣና ምሕረት አርጎ ለቋቸዋል። ማንም እሱ የሚናገረውን የሚያጣጥልና ጎረበጠኝ የሚል አይሰማም፤ ሁሉም ልብ አውቃ ልጅ ነው ይላል።

እሱ ያልተመቻቸው ቢኖሩ የድሮ አለቆቹ ሲዘርፉና ሲሰርቁ የነበሩት ብቻ ናቸው። እናማ የሱን ዲስኩር የሰሙና አገራቸውን የናፈቁ በሙሉ ሸፍተው የከረሙት ሳይቀር አገራቸው ተመልሰዋል። አንተም በዚህ አጋጣሚ አብረህ ትመጣለህ ብለን ብንጠብቅም ችግርህን ስለምናውቀው አልፈረድንብህም። አንድየ ባለው ዕለት ትመጣልናለህ ብለን ተስፋ ሰንቀናል።

እናማ በየቦታው ፍሪዳ እየተጣለ ሕዝቡ ፍቅር አሳይቶ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በዕልልታ ካህናቱ በውዳሴና በዝማሬ፣ ወጣቱም በጭፈራ እየቦረቀ ተቀበላቸው። ባላንጣ ኾነው የቆዩ የጎረቤት አገር ሰዎችም የደስታው ተቋዳሽ ሊሆኑ ችለዋል። ዕድሜና ጤና ለአንተ ይኹንና ልከኽልን በገዛነው ራዲወና ቴሌቢዥን ጧት ማታ እያየን ተጎልተን እንውላለን። ዛሬ ሁሉም ከቴሌቢዥን ላይ ዓይኑን ተክሎ እየዋለ ሥራ ፈት ኹኗል። አንዳንዴማ እረኛውና ገበሬውም ጭምር ሳይቀሩ ቤት ስለሚውሉ ጥጆችና ፍየሎች ታስረው፣ በሬዎችም ተፈተው ይውላሉ።

ደባልቄ!

የኔ ነገር ሥራ መፍታት ስለማልወድ በእርጅና ቦለቲከኛ ኹኘልሃለሁ፤ የአባት አደሩን ረሳሁና ስለ አንተ ጤንነትና ስለ አኗኗርህ ጭምር ጭውውት ማድረግ ሲገባኝ እኔ ለማልገዛው ጉዳይ ቦለቲካ አወራለኹ። ለነገሩማ ቤት መዋሌና ጉልበት ባጣ እንጅ፤ እኔ ያንተ አባት ከማን አንስ ነበር? አሁን አሁንማ የሚነሽጠኝ ድሮ እኛ አገር ስንጠብቅና አካባቢያችን በሽማግሌ ዳኝነትና በጎበዝ አለቅነት ስንመራ በነፍስ ወከፍ የነበረን መሣሪያ ቢበዛ አንድ ፍሻሌ ሽጉጥና አንድ ናስማስር ጠብመንዣ ነበር። አሁን አሁንማ ከክላሽ አልፎ ሃያና ሰላሣ ጥይት የሚጎርስ ጠብመንዣ በየገበያው ይሸጣል። ዋጋው የትየለሌ ባይሆንብኝ እኔም አምሮኝ ነበር። ያው መቸም አንተኑ ማጣፋትና ማስቸገሩ እየከበደኝ እንጅ፤ እኔ አባትህ ጠብመንዣ አያያዝና አተኳኮሱን ከሆነ አምጡ ድገሙ ቢባል የማኮራህ እንጅ የማሳፍርህ አይደለሁም። ቢሆንማ ብትችልና ቢመችህ ሳልሞት አንድ ማለፊያ ዘመናዊ መሣሪያ ብትገዛልኝ ምርቃቴ እስከ ወዲያኛው ይጠብቅኻል። ሌላው ቢቀር ለመቃብር ቤቴ ማሠሪያ ታስበው የነበረውን ትተህ መሣሪያውን ከበቂ ጥይት ጋር ብታደርግልኝ እመርጥ ነበር። ዛሬ ማንም ኸዚህ ውደቅ የማይባለው ሁሉ ዘመናዊ ነፍጥ ሲታጠቅ፤ እኔ የአንተ አባት በአንድ ጎራሽ ናስማስር መቅረብ ሃፈሬታው ለኔ ብቻ ሳይሆን ለአንተና ለሁሉም ልጆቸ ነው። አለበለዚያማ በልበ ሙሉነትና በቆፍጣና ወንድነት ከሆነ ከማንም እልቃለሁ እንጅ የሚበልጠኝ ቀርቶ የሚስተካከለኝም እንደሌለ አውቃለሁ፤ እንዲያው ለእናንተ ኩራትና መከበሪያ ቢሆን ብየ እንጅ።

ደባልቄ!

የእኔ ነገር አንዱን ሳልጨርስ ሌላውን ጨበጥ ለቀቅ እያረኹ መሰለኝ። ስለ ጀመርኩት አዲሱ አለቃ እንዲያውም አሁንማ የሁሉም ሕዝብና የአገሪቱ መሪ ስለኾነ ገና ባይነግሥም መሪያችን ልበለውና የማወጋህን ልብ ብለህ አድምጥ።

ሰውየው እንዳልኩህ አንጎሉ ክፍት ስለሆነ ለሚናገረው ሁሉ አፍህን ክፍት አርገህ አንድትሰማው ያደርግሃል፤ እየዋለ እያደረ ግን ያው ወገንህ እንደምታውቀው የሚያወጋውና ልቡ የሚሸፍትበት ውስጥ ወስጡንና ከራሱ ጋር ስለሆነ፤ የሰውየውን የፍቅር ወግና ዲስኩር ወደ ጉርምርምታ ለውጦታል። ችግር ነው ተብሎ የሚወጋውም ቆራጥና ቆፍጠን ያለ ትእዛዝና ብይን አይሰጥም፤ ወይ ይፈራል አለዚያም አልቻለበትም የሚሉ ሐሜቶች ናቸው። በመሆኑም እሱ ቀን የሠራውን ሌሊት ያፈርሱበታል፣ እሱ ስለ ፍቅር ሲሰብክ ጥላቻንና መበታተንን ሲያስፋፉ ይታያሉ፣ ወንጀለኞቹን በሰላም እጃችሁን ለሕግ አቅርቡ ሲላቸው እነሱ በየቀበሮ ጉድጓዱ ተደብቀው ሕዝቡን ለአመጥ ያነሳሳሉ፣ እሱ ስለ አብሮነትና መከባበር ሲሰብክ እነሱ አሻፈረን ለአንተ አንገዛም ይሉታል።

ይኸውልህ በዚህ መካከል ደግሞ ሌላ የከፋ ነገር መጣ። ምንም እንኳን እኔ ኸዚህ በፊት ሂጀ ባላውቅም ደርሰው የመጡት እንዳወጉኝ አዲስ አበባ የሚባለው የንጉሦቹ መቀመጫ ከተማ እንደ ጣና ሐይቅ የተንጣለለና ያንድ ራሱን የቻለ ምክትል ወረዳ ግዛት የሚያክል ስፋት ያለውና የአገራችን ሰው ከየቦታው ተሰብስቦ የሚኖርበት፣ በሀብትና በሥልጡንነት ብልጡግ የሆነ ከተማ ነው አሉ። የፈረንጁ አገር መንግሥትና እንግዳ ሲመጣ የሚያርፈውም ኸዚያው ነው ይባላል። ነዋሪው ሕዝብ ሸምቶ አዳሪ ነው ቢባልም እንግዳ ሲመጣበት መስተንግዶው ከሞሰቡ ተርፎና ተትረፍርፎ እስከሚነሳ ድረስ ነው ብለው ሲያወጉኝ በአገሬና ወገኔ ኮራኹበት። መቸም ሳልሞት አዲስ አበባን አንድ ቀን እንደምታሳየኝ ተስፋ አለኝ።

ምንም እንኳን በግብርና አይተዳደሩ እንጅ መስተዳድራቸው በራሳቸው ነው ይባላል፤ አሁን እኛ እንኳን በአቅማችን በወረዳው መስተዳድር ሥር እንሁን እንጅ የሚያስተዳድረን ሌላ ሳይሆን የራሳችን ገበሬ ማኅበር ነው። በይፋግ ከተማችን ውስጥም ዕድሩ፣ የሴቶችና የወጣቶች ማኅበር ቢኖርም ኃላፊው ገበሬ ማኅበሩ ሲሆን የገበሬ ማኅበሩ አለቃ ደግሞ ምክትል ወረዳው ነው። በከተማችን ውስጥ የሚገኘው ጥቅማ ጥቅምም በሙሉ ለከተማችንና ለነዋሪው ሕዝቧ ብቻ ነው። አዲስ አበባም ከንቲባ የሚባል የኛን ገበሬ ማኅበር የሚመሳሰል መስተዳድር አለው አሉ።

ታዲያማ እንዲህ እያለ የከተማው ዕድሜ ሲሰላ የአምስትና ስድስት ትውልድ ዕድሜ ነው ይባላል፣ ያውም ኸዚያ ባይበልጥ አይደል? ይህን ዕድሜ እንግዲህ የእኔ ቅድመ አያትና ያንተ ምንዥላት ደርሰውበታል ይባላል፤ አጤ ዳዊት የሚባሉ ንጉሥ ናቸው አሉ የቆረቆሩት፤ ያስኳላ ትምህርት ስለሌለኝ በዘመን ቆጠራ ላይ እምብዛም ነኝና አንተው አስላው።

ይኽውልህ እንዳንተ ፈረንጅ አገር በመኖር አማሪካ ከሚባለው ቦታ የመጣ አንድ ኮበሌ ቢጤ ወጣቱንና ጨዋውን ሕዝብ ሰብስቦ በዲስኩር በማደናገር አዲስ አበባ የእናንተ ብቻ እንጅ ኸዚህ እንጀራ ፍለጋ ለመጡትና ተወልደው ላደጉት አይደለችም፤ እነሱን ማስወጣትና ማባረርም መብት አላችሁ ብሎ ስላነሳሳቸው ከፍተኛ አምባጓሮ በተደጋጋሚ ደርሷል እየተባለ ይወጋል፤ ነፍስም ጠፍቷል አሉ። አምባጓሮ ፈጣሪው ሕዝብ ጎራዴና ገጀራ ይዞ በመምጣት ሲያምሰው እንደሰነበተ በኀዘኔታ ይተረካል። ደግነቱ የአገር ሽማግሌዎችና ነገር አዋቂዎች ደርሰው ለጊዜውም ቢሆን ባያበርዱት ኖሮ ጭንቅ ያለ ችግር ይፈጠር ነበር። ነገራ ነገሩም ገና ስለአለየለት ውስጥ ውስጡን እየታመሰ አሁን ድረስ አለ፤ የቤታችን ራዲወና ቴሌቢዥንም ይኸንኑ ነግረውናል።

በአዲስ አበባው ሕዝብ ወገን ደግሞ አንድ ብልኅና የሕግ አንቀጥ አዋቂ ኸዚህ በፊት የሕዝቡን መብት አስከብራለሁ ብሎ የተሟገተና መንግሥት ተናዶበት ዘብጥያ ለአያሌ ዓመታት ያጎረው አሁን በድጋሜ ሕዝቡ ሲንገላታ ቁሜ አላይም በማለት ዋቢ ጠበቃ ሆኖ ቆሟል ይላሉ። በዚህ ሰው ገጥሞ በጣም ብዙ ሕዝብ አብሮት ቁሟል ተብሎ ይባላል። ይሁን እንጅ ያ ዲስኩር አዋቂና ክፍት አንጎል አለው ያልኩህ መሪ በዚህኛው ሰው ላይ ክፉኛ የሆነ ቅያሜ አድሮበታል እያለ ሰዉና ራዲወን ቴሌቢዥኑ በየገበያውና ሰንበቴው በስፋት ያወጋል። አስማምቶና ድንጋይ አሸካክሞ የሚያስታርቅ ካልመጣ አስጨናቂ የሆነ የሕዝብ ለሕዝብ መራበሽ ይመጣ ይሆናል ብለን በጣም ስጋት ተሰምቶናል። መቸም እውነተኛ ጠሎት ማለት በዚህ ጊዜ ስለሆነ፤ እኔና እናትህም ሕዝቡን አስማማው፣ የመንግሥቱንም አልጋ አጥናው ለማለት ሱባዔ ገብተናል። አንተም ብትሆን መጠለይ አለብህ፤ በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌ ስለሌለ የእናንተ የህጣናቶቹ ጠሎት ነው ይህችን አገር ሊያረጋጋትና ሊጠብቃት የሚችለው።

ሁሉን አዋቂው የሊቦው ጊዮርጊስ አንተም ሆንክ እኛ የምናደርገውን ጠሎትና ምህላ ይስማን! - ዓሜን!

ሳትሰለች ጣፍልን፣ ከቻልክም በስልኪቱ ድምጥህን አሰማን፤

ቸር ይግጠመን!

አባትህ ባላምባራስ ቢተው አደፍርስ፣
እናትህ ወይዘሮ ዓለሙሽ ማንያዘዋል

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ